የነቀምት - ቡሬ የመንገድ ግንባታ አካል የሆነው የክፍል 3 (አጋምሳ - ቡሬ) ፕሮጀክት፣ በአሁኑ ወቅት 66.8 በመቶ የግንባታ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።
84.55 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ይህ የአስፋልት ኮንክሪት ግንባታ፣ በአጠረ ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
በአሁኑ ሰዓት የአስፋልት ንጣፍ፣ የአፈር ቆረጣና ሙሌት፣ የውኃ መፋሰሻ (ድሬኔጅ) እንዲሁም የቤዝ ኮርስ ንጣፍ ሥራዎች በተጠናከረ ሁኔታ እየተከናወኑ ነው። የመንገዱ ስፋት በከተማ 21.5 ሜትር፣ በገጠር ደግሞ 10 ሜትር ሆኖ እየተገነባ እንደሚገኝ ከአስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ከ2.2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቀው ይህ ፕሮጀክት በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ የሚከናወን ሲሆን፤ ግንባታውን ቾንግኪንግ ኢንተርናሽናል ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን (CICO) በማከናወን ላይ ይገኛል። የማማከርና የቁጥጥር ሥራው ደግሞ በኮሪያው ኩንሃ ኢንጅነሪንግና በሀገር በቀሉ ኢትዮ ኢንፍራ ኢንጅነሪንግ በጋራ እየተመራ ነው።
ፕሮጀክቱ ቀደም ሲል በጸጥታ ሁኔታ፣ በወሰን ማስከበር ችግሮች እና በተቋራጭ ለውጥ ምክንያት መዘግየቶች አጋጥመውት የነበረ ቢሆንም፤ አስተዳደሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው የተቀናጀ ጥረት አሁን ላይ በጥሩ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ይህ ስትራቴጂካዊ መንገድ ግንባታው ሲጠናቀቅ ቀደም ሲል ከ4 ሰዓት በላይ ይወስድ የነበረውን የጉዞ ጊዜ ወደ 2 ሰዓት ዝቅ ያደርገዋል።
ይህም አርሶ አደሮች ምርታቸውን በአፋጣኝ ወደ ማዕከላዊ ገበያ እንዲያቀርቡ ከመርዳቱም በላይ፣ የአካባቢውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድገው ይጠበቃል።