በዩኔስኮ በማይዳሰስ የሰው ልጅ ወካይ ቅርስነት የተመዘገበው "የፊቼ ጫምባላላ" የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል፣ ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ወሰንየለህ ስምዖን ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በዓሉ መጋቢት 5 እና 6 2018 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ በድምቀት እንደሚከበር ገልጸዋል። የዘንድሮው አከባበር በዓሉ በዩኔስኮ ከተመዘገበ 11ኛ ዓመቱን የሚይዝ መሆኑንም ኃላፊው ጠቁመዋል።
የፊቼ ጫምባላላ በዓል ወንድማማችነትንና የሕዝቦች አንድነትን የሚያጠናክር በመሆኑ፣ ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ ኢትዮጵያውያን በበዓሉ ላይ ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በዓሉ ከባህላዊ እሴቱ ባለፈ ለሀገር ኢኮኖሚና ለቱሪዝም ዘርፍ የሚያበረክተው አስተዋፅዖ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱንም አቶ ወሰንየለህ አብራርተዋል።
የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ወደ ከተማዋ ለሚመጡ እንግዶች የተለመደውን መልካም አቀባበል እንዲያደርጉ ጥሪ የቀረበ ሲሆን፤ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅም ክልሉ ከፌደራል የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉ ተገልጿል።
በፈቃደአብ አለማየሁ