መገናኛ ብዙኀን ከሀሳብ መግለጫነት ባለፈ ለሀገር ግንባታና ለተቋማት ጥንካሬ መሰረታዊ መሳሪያ መሆን እንዳለባቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ገለጹ።
አማካሪ ሚኒስትሩ "መገናኛ ብዙሃን ለብሔራዊ ጥቅም" በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ በሚገኘው ሀገራዊ ኮንፈረንስ ላይ እንደተናገሩት፣ ከለውጡ ወዲህ በሀገሪቱ አራት ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ይገኛል።
እነዚህም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ፣ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን ማፅናት፣ የአዲስ ትርክት ግንባታ እና የብልፅግና ዕሳቤን ማስረፅ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ብሔራዊ ጥቅም "እኛነታችንን የማስቀጠል ጉዳይ ነው" ያሉት ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል፤ ጉዳዩ የሀገር ሉአላዊነትን እና የግዛት አንድነትን ከማስከበር ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት እንዳለውም አብራርተዋል። መገናኛ ብዙሃን ከሀሳብ መግለጫነት ባለፈ ጠንካራ ተቋማትን ለመገንባት እንዲቋቋሙ መደረጉንም ጠቁመዋል።
ሚዲያዎች አሉታዊና አዎንታዊ ተፅዕኖ እንዳላቸው የጠቆሙት አማካሪው፣ ለሀገር ብሔራዊ ጥቅም መስራት መሰረታዊና የማይታለፍ ነጥብ ሊሆን እንደሚገባ አፅንዖት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀይማኖት ዘለቀ በበኩላቸው፤ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማዕከል አድርገው እንዲሰሩ የድጋፍ እና ክትትል ሥራዎች እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በባለስልጣኑ ተመዝግበው የሚሰሩ ከ300 በላይ መገናኛ ብዙሃን መኖራቸውን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሯ፤ አብዛኞቹ የኢትዮጵያን ሕግና የሙያ ሥነ-ምግባር አክብረው እንደሚሰሩ በመግለጽ፣ የተወሰኑ መገናኛ ብዙሃን ሀሰተኛ ይዘት ያላቸውን ዘገባዎች እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በኮንፈረንሱ ላይ በመገናኛ ብዙሃን ይዘት የአዝማሚያ ግምገማ ቀርቦ ባለድርሻ አካላት ሰፊ ውይይት እያደረጉበት ይገኛሉ።
በሞላ ዓለማየሁ