Search

የባሕር በር ጥያቄ የሉዓላዊነትና የህልውና ጉዳይ ነው፤ ያጣነውን የመመለስ እጥፍ ድርብ መብት አለን፦ ሜጀር ጄነራል ተሾመ ገመቹ

ሓሙስ መጋቢት 03, 2018 74

ሜጀር ጄነራል ተሾመ ገመቹ ሰሞኑን በዓድዋ ድል መታሰቢያ በተካሄደ የፓናል ውይይት ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ በጠላት ሴራና በተሳሳተ ውሳኔ ያጣችውን የባሕር በር የመመለስ እጥፍ ድርብ መብት እንዳላት አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
እንደ ሞሮኮ እና ቬትናም ያሉ ሀገራት የባሕር በርን በነፃ ወይም በልውውጥ በመስጠት የጋራ ልማትን እያረጋገጡ መሆኑን የጠቀሱት ሜጀር ጄነራሉ፣ በተፈጥሮ የኢትዮጵያ መሬት ከቀይ ባሕር ጋር የሚዋሰን እንደነበርና የአሰብ ወደብም የአፋርን ሕዝብ እንዲያገለግል ተደርጎ ከንድፉ ጀምሮ የተዘጋጀ እንደነበር አስታውሰዋል።
የባሕር በር ማጣት ለጸጥታ ችግርና ለኑሮ ውድነት ዋነኛ ምክንያት መሆኑን የጠቆሙት ሜጀር ጄነራል ተሾመ፣ የባሕር በር ጥያቄ የሉዓላዊነት ጥያቄ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
እያንዳንዱ ዜጋ የባሕር በር ያሳጣንንና ሀገራችንን ለማፍረስ የሚሠራውን ጠላት በመንቃት መመከት እንዳለበትም በንግግራቸው አሳስበዋል።
ይህ ጥያቄ የኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የሀገር ሕልውና ጉዳይ መሆኑን በማንሳት፣ የባሕር በር ባለቤትነት ለቀጠናው ሰላምና ለኢትዮጵያ ዕድገት ቁልፍ ሚና እንዳለው ተመላክቷል።
በአበባየሁ ከፈኒ