የ"ፋይዳ" ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ለጸጥታና ደህንነት ተቋማት ሥራ ስኬታማነት ያለው ፋይዳ የላቀ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊሲ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ገለጹ።
በብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ዙሪያ ትኩረት ያደረገ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ለፌደራል፣ ለክልል እና ለከተማ አስተዳደር ፖሊስ አመራሮችና አባላት በአዲስ አበባ እየተሰጠ ይገኛል።
በመድረኩ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል፤ የፌደራል ፖሊስ ተቋሙን በተለያዩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችና አገልግሎቶች እያዘመነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
እነዚህ ዘመናዊ አገልግሎቶች ከ"ፋይዳ" ዲጂታል መታወቂያ ጋር እንዲተሳሰሩ እየተደረገ መሆኑን የጠቀሱት ኮሚሽነር ጄኔራሉ፤ ይህም ወንጀሎችን አስቀድሞ ለመከላከል እና የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል።
በተለይም በወንጀል ምርመራ ወቅት ትክክለኛ ማንነትን በፍጥነት በማረጋገጥ የሕግ ማስከበር አቅምን እንደሚያጠናክር አፅንዖት ሰጥተዋል።
ፖሊስ እስከ ታችኛው የማህበረሰብ ክፍል ድረስ ወርዶ የሚያገለግል ተቋም በመሆኑ፣ ዜጎች የዲጂታል መታወቂያውን እንዲጠቀሙ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ሚናውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ተናግረዋል።
አሁን ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ 38 ሚሊዮን ዜጎች ለ"ፋይዳ" ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ መመዝገባቸው በመድረኩ ላይ ተገልጿል።
በአባዲ ወይናይ