የግንባታ ዘርፉን በከፍተኛ ደረጃ ለማዘመን የሚያስችለውን የ3ዲ ኮንክሪት ፕሪንት ቴክኖሎጂን በርካታ ሀገራት ተግባራዊ አድርገዋል፡፡
አሜሪካ እና ቻይና ቴክኖሎጂውን በመጠቀም በዓለማችን ቀዳሚውን ስፍራ ከያዙ ሀገራት መካከል ናቸው።
ጀርመን፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ካናዳ የ3ዲ ቴክኖሎጂን በግንባታው ዘርፍ በከፍተኛ ሁኔታ እየተጠቀሙበት ይገኛል።
ኢትዮጵያም በዘርፉ ያላትን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከኦስትሪያ ኩባንያ ጋር በመተባበር ወደ ተግባራዊ ምዕራፍ ለመሸጋገር በሂደት ላይ ትገኛለች።
የ3ዲ ኮንክሪት ፕሪንት ቴክኖሎጂ የ3ዲ ሕትመት ቴክኖሎጂን የያዘ ግዙፍ ማሽንን ይጠቀማል። ማሽኑም በኮምፒውተር እየታዘዘ የሚያገኘውን የኮንስትራክሽን ግብዓት ተጠቅሞ ልዩ ልዩ ዲዛይን ያላቸውን ግንባታዎች በእራሱ ያከናውናል።
ግዙፉ ማሽን በተሰጠው ዲዛይን መሰረት ግንባታውን በፍጥነት ማከናወን እንደሚያስችል የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ።
ቴክኖሎጂው የሕንፃ ዶም እና አርቴክቸራክ ጥበባቸው ከፍ ያሉ ግንባታዎች በሚፈለገው ጥራት ማከናወን የሚያስችል መሆኑንም ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
የ3ዲ ኮንክሪት ፕሪንት ቴክኖሎጂ በባህላዊ መንገድ ግንባታ ሲከናወን የሚኖሩ የልስን፣ የብሎኬት ድርደራ እና መሰል የግንባታ ሂደቶችን ከማስቀረቱ ባለፈ የግንባታ ግብዓቶችን ብክነት ይቀንሳል ይላሉ ባለሙያዎች፡፡
ከአካባቢ ጋር የሚስማሙ እና ዝቅተኛ ብክለትን የሚያስከትሉ የግንባታ ጥሬ ዕቃዎችን መጠቀም እንደሚያስችልም በዘርፉ የተከናወኑ ጥናቶች ያሳያሉ።
የ3ዲ ኮንክሪት ፕሪንት ቴክኖሎጂ በርካታ የሰው ኃይል አለመፈለጉ፤ ቀጣይነት ያለው ያልተቋረጠ የግንባታ ሥራዎችን ለማከናወን እንደሚረዳም ባለሙያዎች ይገልፃሉ።
በመሀመድ ፊጣሞ