Search

ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ ያሳካችውን ‘ዲጂታላይዜሽን’ ወደ ቀጣናው ማስፋት ትፈልጋለች፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ዓርብ መስከረም 30, 2018 77

ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘርፍ በሀገር ውስጥ ያሳካችውን ወደ ቀጣናው ማስፋት እንደምትፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ24ኛው የምስራቅ እና የደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ "ኮሜሳ" የመሪዎች ጉባኤ ላይ ገልጸዋል፡፡
በዚህም በዲጂታል ቴክኖሎጂ ትስስር የክፍያ ሥርዓቶቸን በማስፋት እና ፈጠራዎችን በማሳደግ በቀጣናው ሀገራት መካከል ያለውን ትስስር ማጠናከር እንደሚቻል ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቆሙት፡፡
ለዚህም ቀጣናዊ የዲጂታል መሰረተ ልማቶችን ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ ይህን እውን ለማድረግ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ለመሥራት ኢትዮጵያ ዝግጁ ናት ብለዋል፡፡
ዲጂታል ዘርፉን ለቀጣናዊ ትስስር፣ አካታችነት እና ዕድገት አቅም በማድረግ ቀጣናውን ዘመኑ በሚጠይቀው ደረጃ ለማዘጋጀት መሥራት እንደሚያስፈልግ ያመላከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁኑኑ በልበ ሙሉነት፣ በግልጽነት እና በመናበብ መጀመር ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በበኩላቸው፤ ለአፍሪካ ብልፅግና መረጋገጥ ዲጅታል ቴክኖሎጂን የመጠቀም አቅም ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡
አባል ሀገራቱ በዲጂታል ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት የዳታ አመራር እና በሰው ሀብት ልማት በጋራ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጠይቀዋል።
የዲጅታል ቴክኖሎጂ መስፋፋት በቀጣናው ሀገራት መካከል የተሳለጠ የንግድ ግብይት እና አካታች የፋይናንስ ሥርዓትን ለመፍጠር ያስችላልም ብለዋል።
አፍሪካ በዓለም ኢኮኖሚ ትክክለኛውን ቦታ እንድታገኝ፣ ዲጅታል ቴክኖሎጂን ለኢኮኖሚ ሽግግር የመጠቀም አቅም መፍጠር እንደሚገባት ነው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ የተናገሩት፡፡
በለሚ ታደሰ