Search

የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ - ብዝኃ ኃይልን የማስፋፊያ መንገድ

ማክሰኞ ጥቅምት 04, 2018 49

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ለሰላማዊ አገልግሎት የሚውል የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ እንደምትገነባ ይፋ ማድረጋቸው አይዘነጋም።
የሚኒስትሮች ምክር ቤትም የኢትዮጵያ ኒውክለር ኃይል ኮሚሽን ማቋቋሚያ ደንብን አፅድቋል።
የኒውክሌር ኃይል የኢትዮጵያን ብዝኃ ኃይል ማስፋፊያ መንገድ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የሆኑት ደረጄ እንግዳ (ዶ/ር) ናቸው።
ኢትዮጵያ በምትጠቀምባቸው የውኃ እና የንፋስ ኃይል የኤሌክትሪክ ማመንጫዎች ላይ የኒውክለር ኃይል መጨመሯ ከኃይል ሽያጭ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ ይረዳል ብለዋል።
የኒውክሌር ኃይል ከኃይል ማመንጫነት ባሻገር ለሕክምናን አገልግሎት የሚውል በመሆኑ በዘርፉ ተጨማሪ አገልግሎት ለመስጠት ይጠቅማል ሲሉ አስረድተዋል።
በተጨማሪም የኒውክሌር ቴክኖሎጂ እቃዎችን ለማፅዳት፣ ከአፈር እና ከውኃ ጋር የተያያዙ ምርምሮችን ለማከናወን እንዲሁም ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል በመሆኑ ቴክኖሎጂውን መላመድ እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ተግባራዊነትን ለማረጋገጥም ኢትዮጵያ በዘርፉ የሠው ኃይል በማፍራት ላይ እንደምትገኝም ነው የገለፁት።
አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያውያን የዘርፉን ትምህርት በተለያዩ ሃገራት በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ በቀጣይ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ትምህርትን በሀገር ውስጥ በስፋት ለመስጠት ጥናት እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል።
በሴራን ታደሰ