ጆርጂያ ሜሎኒ እ.አ.አ. በጃንዋሪ 15 ቀን 1977 በሮም ጣልያን ነው የተወለዱት።
ወላጅ እናታቸው አና ፓራቶሪ ከባለቤታቸው ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት በመለያየታቸው በወቅቱ የ3 ዓመት ሕፃን የነበረችውን ጆርጂያን እና ታላቅ እህታቸውን አርያናን ለማሳደግ ከባድ መስዋዕትነት መክፈል ነበረባቸው።
በዚህ አይነት መልኩ ሮም ውስጥ በምትገኝ ትንሽ ቤት ውስጥ ከልጅነታቸው አንስቶ በችግር ያደጉት ጆርጂያ ሜሎኒ ከፖለቲካው ዓለም ጋር መተዋወቅ የጀመሩት ገና በ15 ዓመታቸው ነበር።
የጣሊያን ሶሻል እንቅስቃሴ (Italian Social Movement -MSI) የተባለውን የፖለቲካ ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ በመቀላቀል "ሀ" ብለው ፖለቲካውን ተቀላቅለዋል።
ሆኖም ወንዶች የፖለቲካውን መድረክ ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ በተቆጣጠሩበት ቦታ እና ጊዜ የጆርጂያ ሜሎኒን የፖለቲከኛነት ጅማሮ ብዙ ሰዎች በበጎ አልተቀበሉትም ነበር። አንዳንዶቹም በግልፅ ቦታቸው ይህ እንዳልሆነ ይነግሯቸው ጀመር።
ታዳጊዋ ጆርጂያ እንዲህ አይነት አስተያየት ለሚሰጧቸው ሰዎች እየሄዱበት ያለው መንገድ ትክክለኛ እንደሆነ እና አንድ ቀን ጣልያንን እንደሚመሩ ይነግሯቸው እንደነበር የታሪክ ሰነዳቸው ያስረዳል።
ገና በለጋ እድሜያቸው ፓርቲውን ሲቀላቀሉ አንድ ጣልያናዊ ‘አንቺ ልጅ ነሽ ወደቤትሽ ብትሄጂ የተሻለ ነው’ ይላቸዋል፤ ያኔ ታዲያ የጆርጂያ ምላሽ ‘እዚህ የተገኘሁት ሀገሬን ለመምራት ነው’ የሚል ነበር።
ጆርጂያ ችሮችን በመቋቋም ከትምህርታቸው ጎን ለጎን አባል በሆኑበት የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ እየተሳተፉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በዲፕሎማ አጠናቀቁ። ይሁንና በወቅቱ በአቅም ማነስ ምክንያት የኮሌጅ ትምህርታቸውን መግፋት አልቻሉም።
ሆኖም ችግሩ አላማዬ ብለው ከያዙትነገር ሊያግዳቸው አልቻለም። እናም ያለ አባት ያሳደጓቸውን እናታቸውን ለማገዝ የሙዚቃ ሲዲዎችን መሸጥ ጀመሩ።
አዘውትረው ያዳምጡት በነበረውት የማይክል ጃክሰን እና ሌሎች የእንግሊዝኛ ሙዚቃዎች አማካኝነት እንግሊዝኛ ቋንቋን ያለ አስተማሪ መማር ችለዋል።
በአስተናጋጅነት እንዲሁም ሞግዚት ሆኖ በመስራት ሕይወትን ለማሸነፍ እና ቤተሰባቸውን ለመርዳትም ጥረት አድርገዋል። ከዚህ በሚተርፋቸው ጊዜም አባል በሆኑበት ፓርቲ በንቃት መሳተፋቸውን ቀጠሉ።
በፓርቲ ተሳትፏቸው የውይይት ወቅት በበሳል ሀሳብ አፍላቂነታቸው እና በተናጋሪነታቸው ይታወቁ ነበር።
እንዲህ እንዲህ እያለ የሄደው የጆርጂያ ሜሎኒ ሕይወትና የፖለቲካ ጉዞ እያደገ በተለያዩ ሃላፊነቶች መመደብ ችለዋል።
እ.አ.አ. በ1996 ዩዝ አክሽን የተባለውን ብሔራዊ የተማሪዎች ንቅናቄ መምራት ችለዋል።
በ1998 የሮማ ግዛት ካውንስል ሆነው ተመረጡ፣ ጆርጂያ ሜሎኒ ወደዚህ የመጀመሪያዋ በሆነው ይፋዊ የፖለቲካ ሚና መሳተፍ ሲጀምሩ ዕድሜያቸው ገና 21 ነበር።
ከዚያም በ2008 የጣልያን የታችኛው ምክር ቤት የፓርላሜንት አባል በመሆን ተመረጡ።
ጆርጂያ ሜሎኒ በሙሉ አቅምና ጉልበታቸው በፖለቲካው መሳተፋቸውን ቀጥለው እ.አ.አ. በ2008 ልክ በ31 ዓመታቸው በወቅቱ የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩት በሲልቪዮ በርልስኮኒ አማካኝነት የጣልያን የወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ተመረጡ።
በሚኒስትርነት ቦታው ካገለገሉ በኋላም እ.አ.አ. በ2012 የጣልያን ወንድማማቾች ፓርቲ የተሰኘውን የፖለቲካ ድርጅት አቋቋሙ።
አዲሱ ፓርቲ እንደተቋቋመ በሕዝብ ዘንድ በፍጥነት ተቀባይነት አላገኘም ነበር። ሆኖም ህልማቸውን እና ለአገራቸው ያላቸውን ብሩህ ራዕይ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለሕዝቡ በማስረዳት ፓርቲው በሕዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነት እየጨመረ እንዲሄድ ማድረግ ቻሉ።
ጆርጂያ ሜሎኒ በወንዶች ብቻ ተይዞ በቆየው የጣልያን ፖለቲካ መድረክ ላይም እያገዘፉ መጡ።
ከፊት ለፊታቸው የነበሩ የተለያዩ መሰናክሎችን በማለፍ ራሳቸውን በእውቀት እየገነቡ ወደፊት መገስገስ የጀመሩት ጆርጂያ ሜሎኒ፤ የፖለቲካ ጉዟቸው በስኬት ላይ ስኬትን እያስገኘ በ2022 በተደረገው ብሔራዊ ምርጫ በ45 ዓመታቸው የመጀመሪያዋ የጣልያን ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተመረጡ።
ጆርጂያ ሜሎኒ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ከያዙ በኋላ በተለያዩ ዘርፎች ስኬትን ማስመዝገብ መቻላቸው በሕዝብ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት ጨምሮታል።
ደጋፊዎቻቸውም ጆርጂያ ሜሎኒ አገሯን የምትወድ፣ የቤተሰብ ሃላፊ፣ ማኀበራዊ እሴቶችን የምታስከብር እና በአውሮፓ መድረኮች የጣልያን ድምፅ መሆን የቻለች ሲሉ ያወድሷቸዋል።