የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት አጃይ ባንጋ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊነት ለሰጡት ቆራጥ አመራር አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ ከዓለም ባንክ እና የዓለም ገንዘብ ድርጅት ዓመታዊ ጉባኤ ጎን ለጎን ከዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት አጃይ ባንጋ ጋር በዋሽንግተን ተወያይተዋል። ውይይቱ ፍሬያማ እንደነበር የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።
አቶ አሕመድ፣ የዓለም ባንክ በተለይ በቅርቡ ቁልፍ የኢኮኖሚ ሴክተሮችን ለመደገፍ ያዘጋጀውን ከ16 ቢሊዮን ዶላር በላይ የድጋፍ ፓኬጅን በማንሣት፣ ባንኩ ለኢትዮጵያ ልማት ላደረገው ዘላቂ እና ዘርፈ ብዙ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ የጀመረችው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ያስገኛቸው ተጨባጭ ለውጦች ላይም ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠንካራ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የዋጋ ግሽበት መቀነስ፣ የተረጋጋ የምንዛሬ ምጣኔ፣ የወጪ ንግድ ማደጉ፣ የተሻሻለ የውጭ ምንዛሬ ክምችት መኖር የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ያስገኛቸው ተጨባጭ ውጤቶች መሆናቸውን ነው የገለጹት።
ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ መንግሥት ዋና ዋና የልማት ትኩረቶችንም በዝርዝር ያብራሩ ሲሆን፤ እነዚህም፣ የግብርና ትራንስፎርሜሽንን ማስፋት፤ በሰው ኃይል ልማት ላይ ፈሰስ ማድረግ፤ በተለይ በማኑፋክቸሪንግ፣ ኢነርጂ፣ ሎጂስቲክስ እና ዲጂታል ሴክተር ላይ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማሳደግ፤ ፈጠራ የታከለባቸው የፋይናንስ መፍትሔዎችን ማፈላለግ፤ ቀጣናዊ ትሥሥርን ማጠናከር እንደሆኑ ጠቁመዋል።

የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት አጃይ ባንጋ በበኩላቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቆራጥ አመራር በመስጠት የሀገሪቱን የኢኮኖሚ መስመር በእጅጉ በመለወጥ ረገድ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ በማድረጋቸው አድናቆታቸውን እና ምስጋናቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እያካሄደችው ያለው ሀገራዊ ምክክር ማኅበራዊ መስተጋብርን በማጠናከር ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ ይህም ሀገሪቱ እምቅ አቅሟን በማውጣት አካታች እና ዘላቂ ዕድገት እንድታረጋገጥ እንደሚያስችላት ተናግረዋል።
የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን የሪፎርም አጀንዳ እና የትኩረት ዘርፎች ለይቶ በመደገፍ የሀገሪቱ የልማት ጉዞ ተጨባጭ ዘላቂ ለውጥ እንዲያመጣ የሚያደርገውን እገዛ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
በውይይቱ ላይ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ ተክለወልድ አጥናፉን ጨምሮ በአቶ አሕመድ ሽዴ የተመራው ከፍተኛ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን አባላት ተገኝተዋል።