የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር “ዘላቂ የደን ልማት አያያዝና አጠቃቀም” በሚል ዘርፍ ከዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) እውቅና አግኝቷል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ እውቅናውን ያገኘችው በጣሊያን፣ ሮም እየተካሄደ ባለው የዓለም የምግብ ጉባዔ ላይ ነው።
ድርጅቱ ለኢትዮጵያ በ"ዘላቂ የደን ልማት አያያዝና አጠቃቀም" ዘርፍ ዓለም አቀፍ እውቅና የሰጠ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ መንግሥትን ወክለው የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ሽልማቱን ተቀብለዋል።
ሚኒስትሯ በመርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ፋኦ ርሃብን ለማጥፋት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስና የአካባቢ ጥበቃን ለማጠናከር ላለፉት 80 ዓመታት የላቀ ዐሻራ ማሳረፉን አንስተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ዛሬ በምርጥ የዘላቂ የደን ልማት እና ጥበቃ ምሳሌነት እውቅና በማግኘቱ ኮርተናል ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ በብዙ ቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል የደን ሽፋንን ከ17 ነጥብ 2 በመቶ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።
ይህ በመሪ ግልፅ ራዕይ እና በህዝብ ጠንካራ ተሳትፎ የተከወነ እና ተስፋችንን ያለመለመ ስኬት ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ የጉባዔው ተሳታፊዎች ይህን ተጨባጭ ሥራ ወደ ኢትዮጵያ በመጓዝ እንዲጎበኙ እና በዓይን አይተው እንዲመሰክሩ ጋብዘዋል።
ድርጅቱ ከኢትዮጵያ ጋር ላለው ለረጅም ጊዜ የጸና አጋርነት ያመሰገኑት ሚኒስትሯ፤ በጋራ ጥረታችን ችግኞችን እየተከልን የተሻለ ነገን ለልጆቻችን መገንባት ጀምረናል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) ከዚህ ቀደም በምግብ ዋስትና፣ በተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት እና በስንዴ ምርት የላቀ አፈጻጸም ላሳዩት ቁርጠኝነት የከበረውን የፋኦ አግሪኮላ ሜዳሊያ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሸለሙ ይታወሳል።
#ebcdotstream #ethiopia #unfao #fao