ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምታራምደውን ፍትሃዊ የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ዓለም ተረድቶታል ሲሉ የኪንግስ ኦፍ ዓባይ ሚዲያ መስራች እና የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተሟጋቹ ኡስታስ ጀማል በሽር ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
ግብጽ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ መሠረተ ቢስ ክሶችን ማቅረቧን ብትቀጥልም፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግን የኢትዮጵያን የ“ፍትሃዊ የጋራ ተጠቃሚነት” የፀና አቋም በሚገባ ተረድቶታል ብለዋል።
የግብጽ ሚዲያዎች በኢትዮጵያ፣ በዓባይ ወንዝ እና በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ለአረቡ ዓለም የተሳሳተ ትርክት ሲያቀርቡ በመቆየታቸው ግርታ ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያውያንም በቋንቋቸው ጭምር እውነታውን በሚዲያ መግለጥ በመጀመራችን አሁን ላይ ብዥታው እየጠራ መጥቷል ብለዋል።
በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ልዩነታቸውን ወደ ጎን ትተው በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የጋራ አቋም በመያዝ የኢትዮጵያን እውነት ሲገልጡ እና የአንዳንድ አካላትን ሴራ ሲያጋልጡ ስለመቆየታቸው አንስተዋል።
ይህ በአንድነት በመቆም በኢትዮጵያ ላይ የሚቀርቡ መሠረተ ቢስ ውንጀላዎችን የመመከቱ እና እውነትን የመግለጡ ሥራ ወደፊትም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን ኡስታስ ጀማል በሽር ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ አመላክተዋል።
በሀብተሚካኤል ክፍሉ
#ebcdotstream #ethiopia #abbay #GERD #nile #equitableuse