ከዚህ ቀደም ከሀገር በቀል ዕሳቤዎች ይልቅ በውጭ ሃገራት ፓለቲካዊ አስተሳሳቦች ላይ በማተኮራችን ለችግራችን የምንሰጠው መፍትሔ ውጤት ሊያመጣ አልቻለም ሲሉ በወራቤ ዩኒቨርስቲ የምጣኔ ሃብት መምህርና ተመራማሪ መሐመድ ኢሣ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ሁሉም ነገር ኖሯት ያላትን ሃብት በአግባቡ ያልተጠቀመች ሃገር ተደርጋ ትወሰዳለች ኢትዮጵያ፡፡
እንደየሰዉ ዕይታ ቢለያይም ለምን ወደኋላ ቀረን? ለሚለው ጥያቄ ብዙዎች በጋራ የሚያነሱት የጋራ ሕልም ይዞ አለመነሳት፣ አክሱምና ላሊበላ እንዴት ተገነቡ ብሎ አለመጠየቅ እና በዚህም ቁጭት ወደፊት መንደርደር አለመቻል ይጠቀሳሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቀድማ በመሰልጠን በኪነ-ሕንፃ፣ ነፃነትን በማስጠበቅ እና ግብርናን ቀድማ በመጀመር የታወቀች ሃገር ለምን ወደኋላ ቀረች ብሎ መጠየቅ እንደሚያስፈልግ በመደመር መንግስት መጽሐፋቸውም ሆነ በንግግራቸው ያነሳሉ፡፡
በዚህም በቁጭት በመነሳት ሁለንተናዊ ብልፅግናን ማረጋገጥ የሚቻልበትን መንገድ መተለም እንደሚገባ ያስገነዝባሉ፡፡

ወደኋላ ለምን ቀረን? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የተደመረ አቅምን መጠቀም ይጠይቃል ይላሉ ከኢትዮጵያ ሬድዮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የምጣኔ ሃብት መምህርና ተመራማሪው መሐመድ ኢሣ (ዶ/ር)፡፡
ሕብረ-ብሔራዊነታችንን በአግባቡ አልተጠቀምንበትም የሚል ዕሳቤ ያላቸው ምሁሩ፤ በኢትዮጵያ ሰፊ የሰው ኃይል፣ የተፈጥሮ ሃብትና የኢኮኖሚ አቅም ቢኖርም ይህንን አቅም መጠቀም አለመቻላችን ወደኋላ ካስቀሩን ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳል ይላሉ፡፡
በመሆኑም ወደኋላ ባስቀሩን ጉዳችዮች በመቆጨት መስፈንጠር ያስፈልጋል የሚሉት ምሁሩ፤ ዓለም አቀፍ ግንኙነትን ወቅቱ በሚጠይቀው መልኩ በማስኬድ እና የተደመረ አቅምን በመፍጠር ወደፊት መጓዝ እንደሚያስፈልግ ምክረ ሃሳባቸውን ያቀርባሉ፡፡
በሲሳይ ደበበ