Search

ታማኝ ግብር ከፋዮች አዲስ አበባ እንደገና እንድትሰራ አድርገዋል - አቶ አገኘሁ ተሻገር

ሓሙስ ጥቅምት 06, 2018 116

ታማኝ ግብር ከፋዮች አዲስ አበባ ለአፍሪካ ከተሞች ምሳሌ እንድትሆንና እንደገና እንድትሰራ በማድረግ የላቀ ሚና መወጣታቸውን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለታማኝ ግብር ከፋዮች የእውቅና መርሐ ግብር አካሂዷል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ወቅት፤ መንግሥት ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በጥራት እየተገበረ ይገኛል ብለዋል።

ለዚህም የገቢ ሰብሳቢ ተቋማት ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት በቂ ገቢ ለመሰብሰብና ሀገራዊ የልማት ዕቅዶችን ለማሳካት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የፌደራል መንግሥትም ሆነ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢ የመሰብሰብ አቅማቸው እያደገ ነው ያሉት አቶ አገኘሁ፤ በዚህም የማህበረሰቡን ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነት እያረጋገጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ለዚህ ደግሞ የታማኝ ግብር ከፋዮች ሚና ወሳኝ መሆኑን በማንሳት፤ በከተሞች እድገት፣ በወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራና የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ሌሎች ዘርፎች ጉልህ ስኬቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል።

የአዲስ አበባን አዳጊ ፍላጎት በበቂ ደረጃ ለማሟላት የገቢ ሰብሳቢ ተቋማትና ግብር ከፋዮች ይበልጥ ተቀናጅቶ መስራትና ገቢ የመሰብሰብ አቅምን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በገቢ ዘርፍ ሪፎርሙ የታክስ አሰባሰብና አስተዳደር ስርዓትን በማሻሻል የሚሰበሰበው ገቢ እያደገ መምጣቱን ገልጸው፤ ታማኝ ግብር ከፋዮች ለሀገርና ለከተማዋ ልማት ላበረከቱት አስተዋፅኦ አመስግነዋል።