"ከምኞት የማይዘል የድሀ ሀገር ህልም” ተብሎ የተተቸው ፕሮጀክት እውን የሆነበት ምስጢር
ከባንግላዴሽ ዋና ከተማ ዳካ በስተምዕራብ በሚገኘው የፓድማ ወንዝ ዳርቻ ላይ የተገነባው የሩፑር ኒውክሌር ኃይል ማመንጫ እንደዋዛ የሚታይ ቀላል የኮንክሪትና የብረት ክምር ብቻ አይደለም።
ሩፑር ኑክሌር ማመንጫ የባንግላዴሽ የድህነት ዘመን መቋጫ የብሔራዊ ፅናት ምልክት እና ተስፋ መቁረጥን አልቀበልም ያለ የአንድ ሀገር የጀግንነት መዝገብ ነው።
ባንግላዴሽ የኒውክሌር ሃይል ማመንጫ መገንባት ካልቻለች የምታስበውን ዕድገት ማሳካት እንደማትችል የተገነዘቡት መሪዎች ገና በ1961 የኒውክሌር ሃይል ማመንጫ ሊኖር እንደሚገባ የፕሮጀክት ውጥን ሃሳብ ነበራቸው።
በእርግጥ በዚህ ወቅት ስለኒውክሌር ማውራት የሚያስታውሰው አንዱን በሰው ልጅ ህይወት ውስጥ ጥቁር ጠባሳ ስለጣለው የኒውክሌር ቦምብ ብቻ ስለነበር የተወገዘ ቃል ይመስል ነበር።
ኒውክሌር ሳይንስ በሰው ልጅ የምርምር ዘርፍ ውስጥ እጅግ ምጡቅ እና ተፈጥሯዊ የሃይል አማራጮች ላይ ብቻ የነበረውን አተያይ መቀየር የተቻለበት ነው። ይህን ቴክኖሎጂ ግን ለጥፋትም ለልማትም መጠቀም እንደሚቻል ሁሉ በአንድ የታሪክ አጋጣሚ ይህን ቴክኖሎጂ ለክፋት በመጠቀም ብዙ መስራት የሚቻልበትን ቴክኖሎጂ በጥርጣሬ ውስጥ እንዲቆይ በር ከፍቷል።
ይህም ሆኖ ግን ሳይንሱ እና ቴክኖሎጂው የገባቸው ሀገራት ከኒውክሌር የጸዳ ዓለም እንፍጠር እያሉ ቢሰብኩም እነሱ ግን የኒውክሌር ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ከመስራት አልቦዘኑም።
ይህን የተረዱት ባንግላዲሾች ቀድሞ የተጀመረውን የኒውክሌር ሃሳብ በማጠናከር በ1963 በሰሜን ምዕራብ ዳሃካ በጋንጀስ ወንዝ አካባቢ የግንባታ ቦታ በመምረጥ ፕርጀክቱ በመንግሥትም እውቅና የተሰጠው ሆነ።
በወቅቱ ይህች ሀገር የኒውክሌር ሃይል ማመንጫ የመገንባት ፍላጎት እንጂ አቅም የላትም የሚሉ ድምጾች የሚሰሙባት ብትሆንም ነገን አሻግረው የተመለከቱት ግን በውስጥም በውጭም የነበረውን ጩኸት በብልሃት በማለፍ ሥራቸውን ከመስራት አልተዘናጉም።
ባንግላዲሾች ከነጻነታቸው በኋላ 125 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ የሚያመነጭ የኒውክሌር ጣቢያ ለመገንባት በ1980 የጸደቀ ቢሆንም ይህን ዕቅድ እንደገና በመከለስ በ1990 መንግሥት በሩፑር የኒውክሌር ሃይል የመገንባ ጥብቅ ፍላጎቱን በመግለጽ ጉዳዩ ወደፊት እንዲመጣ አድርገዋል።
እዚህ ላይ ባንግላዲሽ የኒውክሌር ግንባታ ላይ ያላት ጽኑ ፍላጎት ማየሉን የተመለከቱ ከምዕራብ ጫና ከምስራቅ ደግሞ እኛ እንስራው የሚል ፍላጎታቸውን የገልጹበት ወቅትም ሆኗል። እናም በ2001 የኒውክሌር ሃይል የድርጊት ዕቅድ ይፋ አደረገች።
በ2005 ደግሞ ሩስያ፣ ደቡብ ኮርያ እና ቻይና ነገሩ ስለገባቸው ፕሮጀክቱን ለመገንባት ቀደም ብለው ፍላጎታቸውን ያሳዩ ሀገራት ሲሆኑ ባንግላዲሽም ከቻይና ጋር የኒውክሌር ትብብር ስምምነት በመፈራረም ጉዳዩ ወደ ተግባር መግባቱን ለዓለም ለመግለጠ ተደርድረዋል።
ባንግላዴሽ የሩፑር የኑክሌር ሀይል ማመንጫ ለመገንባት በወሰነችበት ወቅት ይህን ግዙፍ ፕሮጀክት ለመገንባት የሚያበቃ አቅም ላይ አልነበረችም የሚለው አንዱ የተቃውሞ ድምጽ ነበረ።
በአውሮፓውያኑ 2011 ባንግላዴሽ ከሩሲያ ጋር የሩፑር ኒውክሌር ፕሮጀክት ስምምነት በፈረመችበት ወቅት ሀገሪቱ ከፍተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ የምትሞክርበት ወቅት ቢሆንም ከ40% በላይ የሚሆነው ህዝብ ከድህነት ወለል በታች ይኖር ነበር።
የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት እና ከድህነት ለመውጣት የመሻት ሥራ በኤሌክትሪክ ሃይል ወደኋላ ሊመለስ እንደሚችል የገባቸው የወቅቱ መሪዎች በአንድ በኩል መብራት እንኳን ማግኘት ያልቻሉ ዜጎችን ፍላጎት ለማሟላት በሌላ በኩል ደግሞ የተከፈቱት ፋብሪካዎች እንዳይቋረጡ የሚያስችል ሥራ ላይ እጃቸውን አላቆሙም።
እናም በእንደዚህ አይነት የገንዘብና የሀብት አጥረት ውስጥ ሆኖ የ12.65 ቢሊዮን ዶላር ግዙፍ ፕሮጀክት መጀመር ጥበብን ብቻ ሳይሆን ድፍረት የሚጠይቅ ውሳኔ ነበር።
የባንግላዴሽ ኑክሌር የመገንባት ሀሳብ እንደተሰማ ተቺዎች "ከምኞት የማይዘል የድሀ ሀገር ህልም " በማለት አጣጥለው ነበር። ይሁን እንጂ የባንግላዴሽ መሪዎች መጪውን ዘመን ተመልክተው ዘላቂ እና ርካሽ የኃይል ምንጭ ከሌለ ሀገሪቱ ከድህነት ለመውጣትም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመወዳደር እንደማትችል በማመናቸው ሀገሪቱን ለዘመናት ከነበረችበት የጨለማ ታሪክ ያወጣል ያሉትን ታላቁን የሩፑር ፕሮጀክት አስጀመሩ።
በዚህ ውሳኔ መሰረት ባንግላዴሽ ይህንን በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ታላቅ ፕሮጀክት ስትጀምር በወቅቱ የነበረው የባንግላዴሽ አጠቃላይ አመታዊ የሀገር ውስጥ ምርት ከ100 ቢሊዮን ዶላር ብዙም የማይበልጥ ነበር። ሆኖም ውሳኔው የሀብታምነት ሳይሆን የረጅም ጊዜ የህልውና ጥያቄ ነበርና የነበሩበትን ሁኔታ ወደጎን በማድረግ በይቻላል መንፈስ ታላቁን ፕሮጀክት እውን ለማድረግ መረባረብ ጀመሩ።
በዚህ መልኩ የተጀመረው የባንግላዴሽ የሩፑር የኑክሌር ሀይል ማመንጫ ግንባታ ታዲያ ያጋጠመው የገንዘብ እጥረት ብቻ አልነበረም። በተለይ የፕሮጀክቱ ስራ ተጀምሮ ግማሽ ላይ እንደደረሰ በዓለም አቀፍ ደረጃ አጋጥሞ የነበረው የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ፕሮጀክቱን ለመጨረስ ፈተና ሆነ። በአካባቢው የተፈጠረው ጂኦ ፖለቲካዊ ውጥረት እና የተፈጥሮ አደጋ ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት አደጋ ውስጥ እንዲወድቅ አድርጓል።
ሆኖም እነዚህ ተግዳሮቶች ፕሮጀክቱን ማዘግየት እንጂ ማስቆም አልቻሉምና ባንግላዴሽ ያጋጠሟትን የፋይናንስ፣ የፖለቲካ እና የቴክኒክ ችግሮችን ተቋቁማ በድህነት ወቅት ያለሙትን ህልም እውን ለማድረግ ጠንክረው መስራታቸውን ቀጠሉ።
በዚህ ሁኔታ በብዙ መሰናክሎች መሀከል ሲገነባ የቆየው የአመታት የብርቱ ጥረት ውጤት የሆነው የሩፑር የኑክሌር ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ስራው እየተጠናቀቀ የሚገኝ ሲሆን በዚህ አመት መጨረሻ ላይ ስራ እንደሚጀምር ይጠበቃል።
በቅርቡም ባንግላዴሽ ከኑክሌር ሃይል የምታመነጭ 33ኛዋ ሀገር ሆና ትመዘገባለች።
ይህ የባንግላዴሽ ተሞክሮ ከሀይል ማመንጨት በላይ ነው የዚህች ሀገር ተሞክሮ እንደሚያሳየን ትልቅ ህልምና ራእይ የሰነቁና ይህንንም ለመተግበር የሚያስቡ ሀገራት ፈተናዎችን አልፈው ካሰቡበት ደረጃ መድረስ እንደሚችሉ ማሳያ ነው።
ዋሲሁን ተስፋዬ