ከዳያስፖራው አጀንዳ የማሰባሰብ እና ተወካዮችን የማስመረጥ ሥራ በስኬት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ በደቡብ አፍሪካ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በካናዳ፣ በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ፣ በስዊድን እና በእንግሊዝ የኢትዮጰያ ዲያስፖራ የተሳተፈባቸው መድረኮች አካሂዷል።
በአካል በመድረኮቹ ላይ መገኘት ያልቻሉት በበይነ መረብ መካፈላቸውን የጠቀሰው ኮሚሽኑ፤ በመድረኮቹ የትውውቅ ግንዛቤ፣ የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የተወካዮች ምርጫ መካሄዱን አስታውቋል።
መድረኮቹ አካታችና አሳታፊ እንዲሆኑ የማድረግ ግዴታውን ለመወጣት የሚቻለውን ሁሉ ጥረት ማድረጉን እና ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም መብታቸውን ተጠቅመው በንቃት መሳተፋቸውን ኮሚሽኑ ጠቅሷል።
የሀሳብ ገደብ ሳይኖር ሁሉም እንዲሳተፉ መደረጉን የገለጸው የኮሚሽኑ መግለጫ፤ ወደ አዳራሽ ለመግባት ፈቃደኛ ያልሆኑትም በውጭ ሆነው ሀሳባቸውን መግለጻቸውን አብራርቷል።
ከዳያስፖራው ማኅበረሰብ የተሰባሰቡ አጀንዳዎች ኮሚሽኑ በሚያከናውነው የአጀንዳ ቀረጻ ሂደት ከሌሎች አጀንዳዎች ጋር ተካትተው እንደሚታዩ እና ተወካዮቹም ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ሲካሄድ እንደሚሳተፉ ኮሚሽኑ አስታውቋል።
ከዋና ዋና ተግባራት በተጓዳኝ ልምድ እና ተሞክሮ ለመቅሰምም ጥረት መደረጉን የጠቀሰው ኮሚሽኑ፤ በምክክር እና በሰላም ግንባታ ዙሪያ ከሚሠሩ ተቋማት የተገኙ ልምዶች ኮሚሽኑ ለሚያከናውናቸው ቀጣይ ተግባራት ተጨማሪ አቅም እንደሚሆኑ ጠቁሟል።
በቀጣይ ኮሚሽኑ በአካል ባልደረሰባቸው ሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በበይነ መረብ በመታገዝ አጀንዳቸውን እንዲሰጡ እና ተወካዮቻቸውን እንዲመርጡ የማድረግ ሥራዎች እንደሚሠራም ገልጿል።
ኮሚሽኑ የሀገራቸው ጉዳይ ግድ ብሏቸው በምክክር መድረኮቹ ለተሳተፉ የዳያስፖራ ወገኖች፣ ለተለያዩ የማኅበረሰብ አደረጃጀቶች፣ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ለኢትዮጵያ ኤምባሲዎች እና ሚሲኒዮኖች፣ ለየሀገራቱ መንግሥታት እና በተለያየ መልኩ ድጋፍ ላደረጉ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ምስጋና አቅርቧል።
በሌላ በኩል በትግራይ የምክክር ሂደቱን ለማስጀመር አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች አሁንም ተጠናክረው መቀጠላቸውን ከሚሽኑ ገልጿል።
በትግራይ ክልል ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በሁለት ዙር በተደረጉ ውይይቶች የተገኙ ግብዓቶችን መሠረት በማድረግ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ እንደሆነም አስታውቋል።
እስከአሁን በሕዝባዊ መድረኮችና በልዩ ልዩ መንገዶች የተሰባሰቡ አጀንዳዎችን የማደራጀት እና የማጠናቀር እንዲሁም ለምክክር ጉባዔው አስፈላጊ የሆኑ የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን የማጠናቀቅ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ኮሚሽኑ ጠቁሟል።
#ebcdotstream #ethiopia #የሀገራዊምክክርኮሚሽን #nationaldialoguecommission