Search

ምሥራቅ አፍሪካን ያነቃው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ

ዓርብ ጥቅምት 07, 2018 131

የቲአርቲ አፍሪካ አዘጋጅ የሆነችው ፓውሊን ኦዲያምቦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምሥራቅ አፍሪካን እያነቃ መሆኑን የሚገልጽ ሐተታ አውጥታለች።

ጽሑፏን ስትጀምርም፣ በአፍሪካ ትልቁን ግድብ ያጠናቀቀችው ኢትዮጵያ ኬንያም የራሷን ተመሳሳይ ግድብ እንድትሠራ አንቅታታለች ትላለች።

ታንዛኒያም ሌላ ግድብ ማጠናቀቋን ጠቁማ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎም ሌላ ትልቅ የውኃ ፕሮጀክት ለመገንባት ማቀዷን ጠቅሳለች።

የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ወንዞቻቸውን በማልማት ርካሽ እና አስተማማኝ ኤሌክትሪክ ኃይል እያመነጩ መሆኑን ጠቅሳ፣ ቀጣናውን ከኃይል ጥገኝነት በማላቀቅ የኢንዱስትሪ ዕድገት እውን በማድረግ እና የምግብ ዋስትናን ማረጋጥ እንደሚያስቸለው አትታለች።

ኬንያ ከአበርዳሬ ተራሮች ወደ ሕንድ ውቅያኖስ በሚፈስሰው በታና ወንዝ ለመጀመር አቅዳ ያቋረጠችውን ግድብ ፕሮጀክት መልሳ ለመጀመር መዘጋጀቷም ተጠቁሟል።

ፕሮጀክቱ 5.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ በመያዝ 700 ሜጋ ዋት ኃይል አመንጭቶ አምስት ሚሊዮን ቤቶችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነ ታውቋል።

ኃይል ለአንድ ሀገር ዕድገት ወሳኝ በመሆኑ በትኩረት ሊሠራበት እንደሚገባ የምትጠቅሰው ኦዲያምቦ፣ ይህ ራዕይ ደግሞ ኢትዮጵያ በራሷ ገንዘብ ሠርታ ባጠናቀቀችው በታላቁ የሕዳሴ ግድብ እውን መሆኑን ጠቁማለች።

የቀድሞው የኢሲዮሎ ካውንቲ ምክትል ገዥ መሐመድ ጉሌድ፣ "ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለጎረቤት ሀገራት የኃይል አቅርቦትን ይጨምራል" ማለታቸውንም ጠቅሳለች።

ኬንያ ወደ 800 ሜጋ ዋት የሚጠጋ የኤሌክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ እያስገባች መሆኑን የጠቀሱት ጉሌድ፣ ይህ ለቀጣናዊው የኢነርጂ ደኅንነት ትልቅ እርምጃ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ታንዛኒያ በ2.9 ቢሊዮን ዶላር ገንብታ ያጠናቀቀችው እና ከ2 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የሚያመነጨው የጁሊየስ ኒዬሬሬ ግድብ የቀጣናውን የኃይል ፍላጎት እንደሚደግፍ ጠቅሳለች።

የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያቀረበው ግራንድ ኢንጋ ግድብ ሌላው ሜጋ ፕሮጀክት ለመገንባት መዘጋጀቷን ጸሐፊዋ ጠቅሳለች።

ኮንጎ ለመገንባት ያሰበችው ግድቡ 40 ሺህ ሜጋ ዋት ኃይል የማምረት አቅም እንዲኖረው የታሰበ ነው።

ኡጋንዳ 600 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ ግድብ ለመገንባት በ2024 በፕሬዚዳንቷ ዩዌሪ ሙሴቬኒ አማካኝነት የካሩማ ኃይል ግድብ እየገነባች መሆኑም ተጠቅሷል።

በምሥራቅ አፍሪካ ያለው የግድብ ግንባታ አብዮት ጥቅሙ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማመንጨት በላይ መሆኑን የምትጠቅሰው ጸሐፊዋ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በአየር ንብረት ለውጥ እየተፈተኑ ላሉት ሀገራት የዕድገት ዋስትና መሆኑንም ገልጻለች።  

መዳረሻውም ከኃይል ማመንጨት ያለፈ ቀጣናውን ከኢኮኖሚ ጥገኝነት የሚያላቅቅ ታላቅ ራዕይ መሆኑንም በጽሑፏ አስፍራለች።

በለሚ ታደሰ

#EBC #ebcdostream #GERD #Ethiopia