የሰው ልጅ ከምግብና ግብርና ጋር ያለውን የ500 ዓመታት ጉዞ የሚያሳይ የዓለማችን ልዩ ሙዚየም በጣልያን ሮም ተመረቀ።
የተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) 80ኛ ዓመት ክብረ በዓሉን አስመልቶ በአይነቱ ልዩ የሆነውን የምግብ እና ግብርና ሙዚየም በሮም በዋና መሥሪያ ቤቱ አስመርቋል።
ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ለሕዝብ እይታ ክፍት የሚሆነው እና በአይነቱ ልዩ የሆነው ሙዚየም በውስጡ ቤተ መጻሕፍትን አካቷል።
ቤተ መጻሕፍቱ በግብርና ላይ የሚያተኩሩ እና ከተለያዩ ሀገራት የተሰበሰቡ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ መዛግብትን በውስጡ ይዟል።

በተጨማሪም የተለያዩ የአመጋገብ ባህሎችን እና ከጥንት ዘመን ጀምሮ የነበሩ ባህላዊ የግብርና ዘዴዎችን የሚያሳዩ ሰነዶችንም አካቷል።
እንዲሁም ሳይንስና ቴክኖሎጂ ግብርናውን ለማዘመን የሄዱበትን ርቀት በአንድ ላይ በማጣመር ለጎብኚዎች ግንዛቤን ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀ ነገር መኖሩም ታውቋል።
በጣሊያን ፕሬዚዳንት ሰርጂዮ ማታሬላ እና የፋኦ ዋና ዳይሬክተር ኩ ዶንግዩ በጋራ የተመረቀው ሙዚየም 1 ሺ 300 ካሬ ሜትር ቦታን የሚሸፍን ነው።
በሙዚየሙ ከአርባ በላይ የፋኦ አባል ሀገራት የተለገሷቸው ከ60 በላይ ልዩ የጥበብ ሥራዎች እንደሚገኙም ተገልጿል።
በአይነቱ ልዩ የሆነና የተለያዩ የዓለም ሀገራትን ምግቦች የሚያበስል ማዕድ ቤትንም በውስጡ ያካተተ ነው።
ፋኦ 80ኛ ዓመት ክብረ በዓሉን አስመልቶ “ዘላቂ የደን ልማት አያያዝና አጠቃቀም” በሚል ዘርፍ ለኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር እውቅና መስጠቱ ይታወቃል።
የፋኦ መርሃ ግብሮችን በብቃት በመተግበር ዘላቂ የግብርና እና የገጠር ልማትን፣ የምግብ ዋስትናን እና ፈጠራን ለማሳደግ ባሳየው የላቀ አፈፃፀም ደግሞ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ሽልማት መቀበሉ ይታወሳል፡፡
በዋሲሁን ተስፋዬ