Search

ትናንት የተከሉት ዛሬ የጠቀማቸው ሀገራት

 

በኒውዝላንድ አንዳንድ  ከተሞች አንድ ሰው ትኩስ እንጆሪ  አፕል በለስና  ሌሎችንም ፍራፍሬዎች መመገብ ከፈለገ፤ ከሱ የሚጠበቀው እነዚህ የፍራፍሬ ዛፎች በሚኖርበት አቅራቢያ የት ቦታ እንደሚገኙ ለማወቅ በተዘጋጀው ‘Urban Foraging NZ’  ድረገፅ ገብቶ ማየት ብቻ ነው።

በኒውዝላንድ ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ፓርኮችና ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚበሉ ዛፎችን እና አትክሎቶችን የመትከልና ማኅበረሰቡ በነጻ እንዲመገባቸው የማድረግ ባህል ከተጀመረ ብዙ ዓመታትን አስቆጥሯል።

በዚህ መልኩ በመንግስትና በሕዝብ ተተክለው የበቀሉ ዛፎች ፍሬ በሚያፈሩበት ወቅትሰዎች ወደነዚህ ስፍራዎች በማምራት  የሚያስፈልጋቸውን መጠን ብቻ ወስደው መመገብ ይችላሉ።

ፍራፍሬዎችን የት ቦታ እንዳሉ ከማወቅ ባለፈምእነሱ የተከሉትና ምርት መስጠት የጀመረ የፍራፍሬ ዛፍ ካለም በዚሁ ‘Urban Foraging NZ’ ዌብሳይት ውስጥ ገብተው ቦታውንና የፍራፍሬውን አይነት ማስቀመጥ ይችላሉ።

በኒውዝላንድ ባብዛኛው ከተሞች ይህን መሳይ ባህል የተስፋፋ ሲሆን፤ በተለይ እንደ ኦክላንድ እና ዌሊንግተን በመሳሰሉ ከተሞች የነጻ አትክልቶችንና ፍራፍሬዎችን በማልማት የታወቁ ሆነዋል።

ከኒውዝላንድም በተጨማሪ አንዳንድ ሀገራት በፓርኮች እንዲሁም በመንገድ ግራና ቀኝ በሚገኙ ቦታዎች፤ ይህን መሳይ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ዛፎችን የመትከል ልማድ አዳብረዋል።

ከነዚህም መካከል የጀርመኗ አንደርናች ከተማ ሌላዋ የአረንጓዴ ልማት ምሳሌ ሆና የምናገኛት ናት።

ይህችየምትበላዋ ከተማ” በሚል ቅፅል ስም በምትታወቀው  የጀርመን ከተማ አፕል፣ ሙዝ እና ሌሎች ለምግብነት የሚውሉ እፅዋትን በነጻ መጠቀም የሚቻልባት ከተማ ናት።

በዚህ ከተማ 2010 በተጀመረው ይህ ፕሮጀክት አማካኝነት በመንግስትና በሕዝብ ትብብር ተተክለው ጥቅም የሚሰጡትን እነዚህን ዛፎች የሚንከባከቡ ማኅበረሰባዊ ተቋማት ተደራጅተው ለእነዚህ ዛፎች እንክብካቤ ያደርጋሉ።

ይህ በጎ ጅማሬም ከተማዋን የቱሪስት መስህብ ከማድረግ ባለፈ፤ የጤናማ አመጋገብ ባህልን እያዳበረ ብሎም የአየር ንብረት ለውጥን እየተከላከለ ይገኛል።

ሀገራችን ኢትዮጵያም በጀመረችው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ከተተከሉት ሀገር በቀል እና የተለያዩ ዛፎች ውስጥ 30-40 በመቶ የሚሆኑት ለምግብነትና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ዛፎች እንደሆኑ ይታወቃል።