ከ13 ዓመት በፊት ወደባሌ ዞን ሄደው እንደነበር ያስታወሱት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ፤ በዚያን ወቅት ግን ስለ ባሌ ጥልቅ ዕይታ እንዳልነበራቸው ተናግረዋል።
ሁሉም ነገር እያለ መሠረተ ልማት ባለመሠራቱ ብቻ ይህን እምቅ ሃብት አለመጠቀም የመደህየት ውሳኔ እንደተወሰነ ተደርጎ የሚቆጠር እንደነበር ተናግረዋል፡፡
የሶፍ ኡመር ዋሻም በክረምት ውኃ ሲሞላ ሁሉንም ነገር ጠራርጎ ይወስድ እንደነበር ገልጸው፤ አሁን ግን ዕዳው በሥራ ወደ ሃብት በመቀየሩ ጥፋቱን አስቀርቶ ለልማት ማዋል መቻሉን ገልጸዋል፡፡
ዕዳ የሚሆነውን ተፈጥሮ እንዴት ወደ ሃብት መቀየር እንደሚቻል መታሰብ እንዳለበትም አመላክተዋል።
ቅድሚያ የሚሰጠውን ጉዳይ ለይቶ ወደ ልማት መግባት እምቅ ተፈጥሮን ወደ ሃብት በመለወጥ ሕዝብን ከችግር ማውጣት እንደሚቻል ባሌ ላይ የተሠራው ሥራ ማሳያ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
"አሁን እያወራን ያለነው ስለ ባሌ ብቻ አይደለም" ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ መልማት ያለባቸውን ማልማት ከተቻለ የሕዝብን ትስስር እንደሚያሰፋ ተናግረዋል፡፡
እንደ ባሌ ያሉ እምቅ ሃብት ያለባቸውን አካባቢዎች ከመልክዓ ምድር እና ከታሪክ በላይ የሆነ ሃብት እንዳለባቸው እየታየ ይገኛል ብለዋል።
የተጀመረውን ልማት ለፍፃሜ ለማብቃት በቅብብሎሽ መሥራትን መለመድ እንደሚገባም አመላክተዋል።
ሀገር ምን እንደአላት ማየት መቻል ትልቅ ዕድል መሆኑን ጠቅሰው፤ እርሳቸውም የዚህ ዕድል ተሳታፊ በመሆናቸው እንደተደሰቱ ገልፀዋል፡፡
በለሚ ታደሰ