Search

“የኢትዮጵያን ጸጋዎች እየገለጥን ምን ያህል በሀብት የታደልን መሆናችንን ማየት ጀምረናል” - አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

ማክሰኞ ጥቅምት 11, 2018 54

በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የኢትዮጵያን ጸጋዎች እየገለጥን ምን ያህል በሀብት የታደልን መሆናችንን ማየት ጀምረናል ሲሉ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ተናገሩ።

አምባሳደር ሬድዋን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቀድሞ እና አሁን በሥራ ላይ ካሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በተደረገው “የሶፍ ኡመር ወግ” ላይ ሐሳብ ሰጥተዋል።

በውይይቱ ላይ ባነሡት ሐሳብም፣ “የባሌ ዞንን ሀብት ብቻውን ወስዶ ኢትዮጵያን በሙሉ መቀለብ እና ከኢትዮጵያ የሚትረፈረፍ ሀብትን ለሌሎች ጉዳዮች ማዋል የሚቻልበት አቅም እንዳለ አይተናል” ብለዋል።

ነገር ግን የዚህ ዓይነት የተትረፈረፈ ጸጋ ላይ የተቀመጠ አካባቢ ለዘመናት በሴፍቲኔት ለመቆየት መገደዱ እንደሚያስቆጭም ተናግረዋል።

እንደዚህ ዓይነት ሀብት ይዘን ብዙ መሥራት ሲገባን የተዋደቅንበት፣ የሞትንበት፣ የታገልንበት፣ አሁንም ግማሹ ጫካ የገባበት ምክንያት ለሥልጣን ብቻ መሆኑ አሳዛኝ እንደሆነ ነው የገለጹት።

“እጥረት ያባላል፣ ያጋጫል፣ ያነጫንጫል” ያሉት ዳይሬክተር ጄኔራሉ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ለእኛ በቅቶ ለሌሎች የሚተርፍ ጸጋ እያለን የምንጋጭበት እና እሱ ላይ ተኝተንም ሌላ የምናማትርበት ምክንያት ምን ጋርዶን ነው?” የሚያስብል ነገር እንዳለ አንሥተዋል።

“ሌላውያለውን አንድ ብርቅ ነገር አዋድዶ እና አድንቆ መሸጥ የሚቻልበት ሁኔታ እያለ እኛ የራሳችንን ድንቅ ሀብት ለማወቅም አለመፈለግ፣ ያወቅነውን ማድነቅም አለመፈለግ፣ እሱን ለማልማትም ያልፈለግንበት ምክንያት ‘የትኛዋን ኢትዮጵያ ነበር ታዲያ የወደድናት?’ የሚል ጥያቄ ያስነሣል” ሲሉም ቁጭታቸውን ገልጸዋል። 

ይህንን ሁኔታ ስንመረምረው፣ ድህነትን በውሳኔያችን እና በፍቃዳችን ላያችን ላይ የጫንነው እንደነበር የሚያሳይ ነገር አለው ነው ያሉት።

እንደ አምባሳደር ሬድዋን ገለጻ፣ እንደ ሀገር ያሉንን ጸጋዎች የበለጠ ገልጦ ማየት እና ጥቅም ላይ በማዋል የአንዱን ከአንዱ በማስተሳሰር የበለጠ ለሀገር ዕድገት መሥራት አስፈላጊ ነው።

በዚህ ረገድ በተለየ መንገድ ሀገራችንን እንድናውቅ የጀመርንበት ሁኔታ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገልጸው፣ “ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የወሰዱት ዕይታም፣ አቅምም፣ አተያይም በእጅጉ ጉልህ መሆኑ ዕድለኛ እንድንሆን ያደርገናል” ብለዋል።

በዮናስ በድሉ

#EBC #ebcdotstream #PMAbiy #SofUmar #naturalresource