Search

“እኔ ያሰብኩት፣ እኔ የያዝኩት እና እኔ ያመንኩት ብቻ ልክ ነው” የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፈተና

ረቡዕ ጥቅምት 12, 2018 2589

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሀሳብ አልባ የበቀል ፓለቲካ ከሆነ ውሎ አድሯል የሚሉ ወገኖች ምንአልባትም የአንድ ትውልድ ሂደትን በአንክሮ የተመለከቱ ናቸው፡፡ ይህ ሀሳብ አልባ ፖለቲካ ደግሞ ጽንፈኝነትን ወልዶ ከአንድም ሁለት ትውልድ ስለመብላቱ ዛሬም አብረውን ሆነም የሚመክሩን አልጠፉም፡፡

በሃምሳዎቹ  እና ስልሳዎቹ የጀመረው "የእኔ ሀሳብ ብቻ ምርጥ ነው" አካሄድ "አንባቢ ትውልድ ነኝ" ብሎ ሲያስብ በነበረው ትውልድ እንኳን ሲያቀነቅነው በነበረው ተመሳሳይ ርዕዮተ ዓለም ሳያስማማ ለሀገር የሚጠቅም አንድ ትውልድ በልቶ አልፏል፡፡

"እናሸንፋለን" እና "እናቸንፋለን" የመሳሰሉት ታሪካዊ ስህተቶች ያገዳደለው ትውልድ በከተማ ጦር ተመዝዞ ተገዳድሎ፣ የከተማ ጦርነቱ አላዋጣ ሲል ወደ ጫካ አምርቶ በጫካም በርካቶችን የጥይት እራት አድርጎ የሴራ ድር ማድራቱን ቀጠለ፡፡

ከከተማ እስከ ጫካ የቀጠለው በአንድ ዓላማ ሥር ተሰልፈው ሃሳብ ለማንሸራሸር የፈለጉትን ግማሹን በልቶ ሌሎቹን ማሰደዱን ለማየት ብዙ መጽሐፍ ማገላበጥ የሚጠይቅ አይደልም ይልቁንም ሕወሓት በጫካ እያለ በአንድ ሌሊት የፈጃቸው እና በተአምር ሕይወታቸው ተርፎ በስደት የኖሩት ፖለቲከኞች ለዚህ ምስክሮች ናቸው። በእርግጥ ፖለቲከኛ ማነው ብሎ ለሚጠይቅ ሰው መልስ መስጠት በሚቸግርበት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከሴራ ያለፈ መግደል እና መገዳደል መለያው እስኪመስል ብዙ ዓመታትን ተጉዘንበታል።

እንዲህም ሆኖ የበላውን በልቶ ያጠፋውን አጠፍቶ በኢትዮጵያውያን  መቃብር ላይ የተመሰረተው መንግሥት የነበረውን ተስፋ ሳይሆን ሌላ የሀገር መከራን አዋልዶ 17 ዓመታት ሺህ ወጣቶችን በልቶ ጥቂቶችን ወደ ሥልጣን ቢያመጣም የሃሳብ ልዕልናን ማምጣት ግን አልቻለም። ዛሬም ተስፋ ይመጣል ብለው ይጠብቁ የነበሩትን ተስፋ አሳጥቶ እሱም ተጠናቆ ሌላ 27 ዓመታት ሴራን ተክቶ የለመደውን ትውልድ የመብላት መንገድ ይዞ እዚህ ደርሷል፡፡

"የኔ ብቻ ሃሳብ ምርጥ ነው" የሚለው አካሄድ ጽንፈኝነት ወልዶ ሌሎች ጫካ ናፋቂዎችን አፍርቶ ሀገርን ፈተና ውስጥ እንድትቆይ አስገድዷታል፡፡ ዛሬ በበርካታ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ጽንፈኝነትን ፈልፍሎ ሕዝብ መከራውን እንዲገፋ እያደረገ ያለውን ችግር የተወለደው ከዚህ ከረጅም ጊዜ የ”እኔ አውቅልሃለሁ” የጸረ ዴሞክራሲያዊ ልምምድ ነው፡፡

ዓለም ወደ አምስተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት እየተሸጋገረች ባለችበት በአሁኑ ወቅት በአዳራሽ ውይይት ሊፈቱ የሚችሉ የፖለቲካ ልዩነቶች ሁሉ ጠመንጃ አስነክሰው ወደ ጫካ የሚያስሮጠው ይኸ ልክፍት ነው፡፡

ትምህርት ቤቶችን በመዝጋት፣ የሕዝብ ተቋማትን በማውደም፣ በሃሳብ ልዩነት ሰዎችን መፈረጅ እና ማሰቃየት፣ ከባዳ ጋር ተባብሮ በባንዳ ሀገርን መውጋት፣ በአመጽ የፈረሱ ሀገራትን እንደምሳሌ በማንሳት ያንን መንገድ ለሀገር መመኘት እና ሌሎች ጽንፍ የረገጡ እንቅስቃሴዎች "እኔ ብቻ ትክክል ነኝ" አስተሳሰብ ውጤቶች ናቸው፡፡

"የሌሎችን እውነታ፣ ሁኔታና አመለካከት ወደ ራስ ወስዶ ለመመልከትና ትኩረት ለመስጠት አለመቻል ወይም አለመፍቀድ፤ ሌሎች አማራጮችን ለመቀበል አለመፈለግ፤ ሁልጊዜእኔ ያሰብኩት፣ እኔ የያዝኩትና እኔ ያመንኩት ብቻ ልክነውብሎ ማመን፤ በጥቅሉየእኔ የሆነ ነገር ሁሉ ትክክል ነውብሎ ማሰብ፤ ሌሎች ከእኛ አስተሳሰብ ውጪ ያሉ ሰዎችን በአንድ ቅርጫት ውስጥ የመከተት እና የመፈረጅ ዝንባሌ መኖር" ነው። (የመደመር መንግሥት ገጽ 366)

"ከእኔ ጋር ካልሆነ ከጠላቴ ጋር ነው" ብሎ መፈረጅ፤ አደገኛውን እና የመጨረሻውን ደረጃ ደግሞ፤ የአመለካከት ወይም የአስተሳሰብ ጽንፍን በቀጥታ ወደ ተግባር መቀየር እንደሆነም  በመጽሐፉ ተገልጿል።

ይህ ደግሞ በፖለቲካ ገበያ ውስጥ ቡድኖች የግል እና የቡድን ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም ጽንፈኝትን መመርኮዣቸው ማድረጋቸውን ማሳያ እንደሆነ ተጠቅሷል።

ጽንፈኝነት ደግሞ ግብ ሳይሆን ወደ ጥቅሞች በሚደረግ ጉዞ መጓዣ ምርኩዝ በመሆን አገልግሎት እንደሚሰጥ የሚጠቅሰው መጽሐፉ፣ ጽንፈኝነት የሚሠራበት እና የሚቆምበት ብሎም የሚራመድባቸው ማኅበረሰባዊ ቡድኖች እንደሚፈልግ ይገልጻል።

በአንድ ቡድን ያሉ ግለሰቦች በተናጠል ከሚኖራቸው የጽንፈኝነት አዝማሚያ ይልቅ ቡድኑ በድምር የያዘው የጽንፈኝነት አዝማሚያ አደገኛ እንደሆነ የሚጠቅሰው የመደመር መንግሥት፣ በቡድን መወሰን በግል ከመወሰን ያነሰ አመክንዮ እና የባሰ መድሎ እንዳለው ያስቀምጣል፡፡

በቡድን የሚሰባሰቡ ሰዎች በመርሕ፣ በአመከንዮ እና በዴሞክራሲ እስካልተመሩ ድረስ፣ ለራሳቸው ቡድን የተለየ ቦታ መስጠት እንደሚጀመሩም በጥናቶች መረጋገጡን በመጽሐፉ ላይ ተጠቅሷል።

እነዚህ በቡድን የሚሰባሰቡ አካላት ቡድናቸውን በመርሕ፣ በአመክንዮ እና በዴሞክራሲ ከመመሥረት እና ከማኖር ይልቅ፣ ለሌሎች ቡድኖች ባለ ጥላቻ፣ ተቃርኖ እና ትግል እየመገቡ እንደሚያቆዩትም ያወሳል።

"ብዙ ሰው አለ፤ ሐሳቡ የብዙዎች ነው፤ እኔ ብቻዬን አላጠፋሁም፤ ችግር ከመጣ በጋራ እንጠየቃለን" የሚሉ ስሜቶች እና ጽንፈኝነት በቡድን ውስጥ እንዲጸና እና ግለሰቦች ከተጠያቂነት እንዲሸሹ እንደሚያደርጉ ነው የተጠቀሰው።

እንደዚህ ዓይነት አካሄዶች ናቸው ከትውልድ ትውልድ እየተወራረሱ በዚህ ሰዓት የእምነት ተቋማትን፣ ትምህርት ቤቶችን እና ሌሎች ሕዝባዊ ተቋማትን ሳይለይ እየፈተነ ኢትዮጵያንም ዋጋ እያስከፈላት ያለው፡፡

በለሚ ታደሰ