የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ከዓለም ባንክ ግሩፕ እና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ዓመታዊ ስብሰባዎች ጎን ለጎን በጤና ሥራ አመራሮች ጥምረት ስብሰባ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
በመድረኩ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ የጤና ሽፋን (ዩኤችሲ) ፕሮግራም ከተመረጡ ስምንት አገሮች አንዷ መሆኗ ይፋ ተደርጓል።
በዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት እና በዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የተዘጋጀው ውይይቱ፤ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎትን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከሩ ታውቋል።
በወቅቱ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ፣ ኢትዮጵያ ጠንካራ የጤና ሥርዓትን ለመገንባት ያስቀመጠችውን ስትራቴጂያዊ ዕቅድ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ሽፋንን ከማስፋፋት ባሻገር በጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማጠናከር ይበልጥ እየሰራች መሆኗንም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያን የጤና ዘርፍ ለመቀየር አራት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት መደረጉን አስታውቀዋል።
እነዚህም የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ሽፋን ማስፋፋት፣ ኢትዮጵያን በጤና ደኅንነት ረገድ ቀጣናዊ መሪ ማድረግ፣ በቀጣዮቹ 3 ዓመታት ለጤና ዘርፍ የሚወጣውን ወጪ ውጤታማነት በ20 በመቶ ማሳደግ እና በጤና አገልግሎት አሰጣጥ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማጠናከር መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ሚኒስተሩ ኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የፋርማሲዩቲካል ምርት አቅሟን እና በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ማዕቀፍ ስር የወጪ ንግድ ዕድሎችን ለመጠቀም ያላትን እምቅ አቅም አሳይተዋል።
ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ሽፋንን በማስፋፋት ረገድ አመርቂ ውጤት ማሳየቷን አመላክተው፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች በጤና ዘርፍው ላይ ጫና እያሳደሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በጌትነት ተስፋማርያም