Search

በጋምቤላ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሥራ ጀመረ

ረቡዕ ጥቅምት 12, 2018 55

በጋምቤላ ክልል ጋምቤላ ከተማ የተገነባው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተመርቆ ሥራ ጀምሯል፡፡
የኢፌዴሪ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር)፣ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ እና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በጋምቤላ ከተማ የተገነባውን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል፡፡
ማዕከሉ ዘመናዊ አሰራርን በመከተል የተገልጋዮችን እርካታ የሚፈጥር እና የተሳለጠ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት ተናግረዋል፡፡
ዜጎች ከመንግስት ተቋማት የሚያገኙትን መሠረታዊ አገልግሎቶች በማዘመን የተገልጋዮችን እርካታ ለማሟላት የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውንም አክለው ገልጸዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ፤ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የማህበረሰቡን ፍላጎት የሚያሟላ ከሙስናና ብልሹ አሰራር የፀዳ አገልግሎት ለመስጠት የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የማዕከሉ መገንባት የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል ለማግኘት የሚያስችል በመሆኑ፣ ወጪን በመቆጠብ እንግልትን የሚቀንስ ስለመሆኑም አክለዋል፡፡
ተቋሙ ካሁን በፊት በአገልግሎት አሰጣጥ ዙርያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ፣ የአገልግሎት አሰጣጡን የበለጠ ለማዘመን እንደሚያግዝ ነው የተናገሩት፡፡
በሚፍታህ አብዱልቃድር