Search

ተክሎችን ውሃ ለማጠጣት ምቹው ሰዓት የቱ ነው?

'የማይንከባከቡት ችግኝ፤ ልጅ ወልዶ እንደመጣል ይቆጠራል' ይባላል። ኢትዮጵያውያን በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተከሏቸውን ችግኞች የመንከባከብ ሃላፊነቱ እንዳለባቸው በተለያዩ አጋጣሚዎች ይነገራል።

ከእንክብካቤዎቹ መካከል ደግሞ በተለይ መኮትኮት እና የውሃ የማጠጣት ተግባራት ዋናዎቹ ናቸው። ሁሉም ተክሎችም አንድ አይነት ባህሪ ስለሌላቸው አንዳንዶቹ ውሃ ሲያጡ ቅጠላቸው ሲጠወልግ ሌሎች ተክሎች ደግሞ ምንም ምልክት ላያሳዩ ይችላሉ።  

ተክሎችን ከሚገባው በላይ ማጠጣትም ሆነ ከሚገባው በታች ማጠጣት ሥሮቻቸው እንዲዳከሙ፣ ቅጠሎቻቸው የማይፈለግ ቀለም እንዲይዙ፣ አበባዎቻቸው እንዲረግፉ ወይም እንዳያብቡ ሊያደርግ ይችላል ይላሉ ባለሙያዎች።

ለመሆኑ ተክሎችን መቼ ውሃ ማጠጣት ይገባል?

ባለሙያዎች እንደሚመክሩት ጠዋት ላይ ተክሎችን ውሃ ማጠጣት ለቀኑ ውሏቸው ያዘጋጃቸዋል። ምሽት ላይ ማጠጣት ደግሞ ቅዝቃዜን ይሰጣቸዋል።

ከሁሉም በላይ ጠዋትና ማታ ማጠጣት ተክሉ ውሃን ይዞ እንዲቆይ ይረዳዋል። ከሰዓት በኋላ በተለይም በበጋ ወቅት በቀጥር ሰዓት ተክሎችን ውሃ ካጠጧቸው ግን ፀሐዩ በከፍተኛ ደረጃ ላይ ስለሚሆን ውሃው ወደ አፈር እና ሥሮች ከመድረሱ በፊት እንዲተን ያደርገዋል።

በመሆኑም ጠዋት እና ምሽት ላይ ተክሎችን ውሃ ለማጠጣት ተመራጭ ጊዜያት መሆናቸውን የማሳቹሴት ዩኒቨርሲቲ ጥናት ያመለክታል። ምሽት ላይ ከሚደረግ የውሃ ማጠጣት ተግባር ደግሞ ጠዋት ላይ ማጠጣቱ ይበልጥ ይመረጣል።

ምክንያቱም በምሽት ተክሎች ውሃ ሲያገኙ በአፈር ውስጥ፣ በሥሮች ዙሪያ እና በቅጠሎች ላይ ውሃው ሳይተን የመቆየት ባህሪ ስላለው ለፈንገስ እድገት እና ለነፍሳት መስፋፋት ምቹ ሁኔታን ሊፈጥር እንደሚችል ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

በመሆኑም በማታ ውሃ ሲያጠጡ እጅግ መጥኖ እና ተክሉ ቅጠልና ግንድ ላይ እንዳያርፍ አድርጎ መሆን እንዳለበት ጥናቶች ያመለክታሉ።

ከዚህ ባለፈ ግን የጠዋት የውሃ ማጠጣት ተግባር እና የተለያዩ እንክብካቤዎችን ማዘውተር ለተሻለ የተክሎች እድገት ወሳኝ መሆኑን ባለሙያዎች ይመክራሉ።