Search

አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ - የአርሶ አደሩ አጋዥ ኃይል

ዓርብ ጥቅምት 21, 2018 74

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በብዙ ሀገራት የሚገኙ አርሶ አደሮች እጃቸው ላይ ባለው ስልክ ወይም በኮምፒውተራቸው አማካኝነት በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ወይም ሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን ታግዘው ስለ እርሻቸው አስፈላጊና ወቅታዊ መረጃዎችን በማግኘት ተጠቃሚ እየሆኑ ነው።

ይህ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ የአየር ሁኔታ መረጃዎችን፣ የግብርና ባለሙያዎችን ልምድ፣ ከአርሶ አደሮች የተሰበሰበውን መረጃ እንዲሁም ከሳተላይትና ጂፒኤስ (GPS) የሚገኙ አስፈላጊ መረጃዎችን አጠናቅሮ ጠቃሚ ምክሮችን የሚሰጥ ሲሆን፣ ኢንተርኔት ባለበት ቦታ ሁሉ አገልግሎት ይሰጣል።

ለምሳሌ፣ በዚህ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሆነ አርሶ አደር የአፈር ማዳበሪያ ከመጨመሩ በፊት መረጃ ለማግኘት ቢሞክር ወይም የሰብሉን ጤንነት ማወቅ ቢፈልግ፣ አስፈላጊውን የምስል እና የተለያዩ መረጃዎችን በስልኩ በመላክ መረጃ ማግኘት ይችላል።

አገልግሎት ሰጪዎችም ከሳተላይትና ከመሰል የግብርና ተቋማት በሚያሰባስቡት መረጃ መሠረት፣ "በቀጣይ ሁለት ቀናት ዝናብ ስለሚኖር ማዳበሪያውን ነገ ብትጨምር የተሻለ ጥቅም ታገኛለህ" ወይም "የእርሻህ ምስል እንደሚያሳየው በተወሰነ ክፍል የፈንገስ በሽታ ሊጀምር ነውና በፍጥነት መፍትሔ መፈለግ ይኖርብሃል" የሚል ምክር ሊሰጡ ይችላሉ።

ይህ ብቻ አይደለም። የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂው በተለይ በመስኖ ለሚለሙ ማሳዎች ምን ያህል የውኃ መጠን እንደሚያስፈልጋቸው መረጃ በመስጠት የውኃ ብክነትን ይቆጣጠራል።

ቴክኖሎጂው ከሳተላይት በሚገኙ ወቅታዊ ምስሎች እንዲሁም በእርሻ ቦታው ላይ ወይም በትራክተሮች ላይ በተገጠሙ ትናንሽ መረጃ ሰብሳቢ ቁሶች አማካኝነት የሰበሰበውን መረጃ መሠረት በማድረግ ምን ያህል ማዳበሪያ መጠቀም እንደሚገባ ትክክለኛውን መረጃ በመስጠት ብክነትን በመቀነስ ረገድም ጠቃሚ ነው።

በአፈር ውስጥ የሚገኘውን የንጥረ ነገር ይዘት በመፈተሽ፣ የምርት ሁኔታን በመገምገም፣ የሰብል በሽታ እና ተባዮችን አስቀድሞ በመጠቆም የምርት ጥራትና ምርታማነትን ለማሳደግም ቴክኖሎጂው አይነተኛ መፍትሄ ሆኗል።

ትክክለኛውን የአየር ንብረት በመተንተን አርሶ አደሮች መቼ መዝራትና ምርት መሰብሰብ እንዳለባቸው መረጃ ይሰጣል።

በአጠቃላይ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ባህላዊውን ግብርና ወደ ዘመናዊ በመቀየር ዘርፉ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተስማማ እና ትርፋማ እንዲሆን እየረዳ ይገኛል።

የሰው ሰራሽ አስተውሎት ለግብርናው ዘርፍ የሚሰጠውን ጠቀሜታ በመረዳትም ኢትዮጵያ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አማካኝነት መሰል አገልግሎቶችን የሚሰጥ "ፋርመር ዶት ቻት" የተሰኘ ‘ቻት ቦት’ ወደሥራ በማስገባት ለአነስተኛ ገበሬዎች ዘመናዊ ግብርና ነክ ምክሮችን በመስጠት እየሠራ ይገኛል።

በዋሲሁን ተስፋዬ

#EBC #ebcdotstream #AI