የዓለም የሙቀት መጠን መጨመር በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ ያሉ ከተሞች የሙቀት መጠን እንዲባባስ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህም ለነዋሪዎችም ለአሽከርካሪዎች አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ የመንገድ መሰረተ ልማቶች ያለጊዜያቸው እንዲያረጁ ምክንያት ሆኗል፡፡
ኳታር በከተሞች ውስጥ በተሰሩ የመኪና መንገዶች እየጨመረ ያለውን የሙቀት መጠን ለመቀነስ ታዲያ አዲስ የፈጠራ ስራ ተግባራዊ ማድረግ ጀምራለች፡፡
ሀገሪቱ ሰማያዊ ቀለም ያላቸው መንገዶችን በመጠቀም የሙቀት መጠንን በ20 ዲግሪ ሴልሺየስ መቀነስ ችላለች፡፡
የፀሃይ ብርሃንን መልሶ የሚያንፀባርቅ ቁሳቁስ በመጠቀም የመኪና መንገዶችን ሰማያዊ ቀለም እንዲኖራቸው በማድረግ ኳታር የጀመረችው ሙከራ ሙሉ በሙሉ ከተሳካ ወደፊት ለኑሮ ምቹና ዘላቂነት ያላቸው ከተሞችን እውን ለማድረግ ጠቃሚ ነው ተብሏል፡፡
የመኪና መንገዶች ሰማያዊ ቀለም እንዲኖራቸው መደረጉ ከፀሃይ የሚመጣው ጨረር በመንገዱ ውስጥ ቆይቶ ከፍተኛ ሙቀት እንዳይፈጥርና ተመልሶ እንዲንፀባረቅ በማድረግ የመሬቱን የሙቀት መጠን ለመቀነስ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል፡፡
በዚሁ ትግበራ መሰረት ኳታር በዋና ከተማዋ ዶሃ አንዳንድ መንገዶች ላይ ያከናወነችው ሙከራ የመሬቱን አማካይ የሙቀት መጠን በ20 ዲግሪ ሴልሺየስ መቀነስ እንዳስቻለ ተነግሯል፡፡
እንደ ኢኮሜና ዘገባ ሰማያዊ ቀለም ያለው መንገድ አማካይ የሙቀት መጠን ከሌላው መደበኛ መንገድ በ20 ዲግሪ ሴልሺየስ ሙቀቱ ዝቅ ያለ መሆኑም ነው የተመላከተው፡፡
የሙቀት መጠኑ መቀነስ መቻሉ የመንገዱን ዉበት ለመጨመር፤ ቶሎ እንይበላሽ እና ለጥገና የሚወጣውን ወጪ ለመቀነስ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል ተብሏል፡፡
ኳታር ለሙከራ ተግባራዊ ያደረገችው የመኪና መንገዶችን ሰማያዊ ቀለም እንዲኖራቸው የማድረግ ቴክኖሎጂ ይበልጥ ውጤታማ መሆኑ ከተረጋገጠ በመላው ዓለም በከፍተኛ ሙቀት ለሚቸገሩ ከተሞች ፍቱን መፍትሄ ሊሆን እንደሚችልም ተገልጿል፡፡
በላሉ ኢታላ
#ebc #ebcdotstream #Qatar #temperature #Blue_colored_roads