ቻይና ‘T1400’ ስትል የሰየመችው አዲስ ሰው አልባ ሄሊኮፕተር የሙከራ በረራውን በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቁ ተዘገበ።
ሰው አልባ ሄሊኮፕተሩ እስከ 650 ኪሎ ግራም ክብደት ያላቸውን ቁሶች ወይም ተሳፋሪዎችን ይዞ የመብረር አቅም እንዳለውም የተገለጸ ሲሆን፤ ለተከታታይ 8 ሰዓታትም መብረር እንደሚችል ተጠቁሟል።
‘ሀርቢን ዩናይትድ ኤርክራፍት ቴክኖሎጂ’ ያመረተው ይህ ሰው አልባ ሄሊኮፕተር፤ በሰሜናዊ ምስራቅ ቻይና በሃርቢን ከተማ በቅርቡ ያደረገው የመነሳት፣ የማረፍ እና የመብረር እንቅስቃሴ የተሳካ ነበር ተብሏል።
ሰው አልባ ሄሊኮፕተሩ የመጀመሪያ በረራውን በተሳካ ሁኔታ ማካሄዱ ለቻይና አቪዬሽን ዕድገት ትልቅ እርምጃ ነውም ተብሏል።
ከባድ ከባቢን እንዲቋቋም ተደርጎ የተመረተው ሰው አልባ ሄሊኮፕተሩ ከ40 ዲግሪ ሴሊሺየስ እስከ 55 ዲግሪ ሴሊሺየስ ያለ የሙቀት መጠን እና ኃይለኛ ንፋስን እንደሚቋቋም ተገልጿል።
ሰው አልባ ሄሊኮፕተሩ ሰፊ የእርሻ መሬቶችን ለመንከባከብ፣ ደኖችን፣ ሐይቆችን እና ወንዞችን ለመጠበቅ፣ ቁሶችን ከቦታ ቦታ ለማጓጓዝ እና ድንገተኛ አደጋ የማዳን ሥራ ለመስራት ያለመ መሆኑም ተነግሯል።
በቀጣይ ቻይና ሰው አልባ ሄሊኮፕተሩን በብዛት አምርታ ጥቅም ላይ የማዋል ፍላጎት እንዳላትም ሲጂቲኤን ዘግቧል።
በሰለሞን ከበደ