እንደ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ከሆነ በጡት በማጥባት በየዓመቱ ከ820 ሺ በላይ ሕፃናትን ሕይወት መታደግ ይቻላል።
የጡት ማጥባት ግንዛቤን ለማዳበርም በየዓመቱ በዓለም እና ሃገር አቀፍ ደረጃ የጡት ማጥባት ሳምንት ከሐምሌ 25 እስከ ለነሐሴ 1 ድረስ በልዩ ልዩ ግንዛቤ መስጨበጫ ፕሮግራሞች ይከበራል፡፡
በኩዋም ዶክተርስ ዊዝ አፍሪካ የሕፃናት ሃኪም የሆኑት ዶክተር ሄኖክ ዘውዱ፤ ሕጻናትን ስናሳድግ ለመጀመሪያዎቹ 6 ወራት የእናት ጡት ወተት ብቻ ያስፈልጋል ሲባል ሐኪም ካዘዘው መድሃኒት ውጪ ውሃም ቢሆን መስጠት እንደማይገባም አስገንዝበዋል።
አንዲት እናት ከስድስት ወር በኋላም ቢያንስ እስከ 2 ዓመት ድረስ ከተጨማሪ ምግብ ጋር ልጇን ጡት ማጥባትን መቀጠል እንዳለባት አንስተዋል።
የእናት ጡት ወተት በተፈጥሮ የተገኘ ምንም አይነት ወጪን የማይጠይቅ፣ የጨቅላ ሕፃናት እና የሕፃናት ምግብ ነው ይላሉ፡፡
እናቶች ጨቅላ ሕጻናትን ጡት በማጥባት ጤናቸውን እንዲጠብቁ በየጊዜው ማበረታታት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
የእናት ጡት ለሕጻናት እድገት አስፈላጊ የሆኑትን ንጥረ ነገሮች እና ኃይል ስለሚሰጥ የምግብ እጥረትን እና የምግብ አለመመጣጠን እና ሌሎች ችግሮችን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ይላሉ።
ጡት ማጥባት በየትኛውም የኑሮ ደረጃ ላይ የምትገኝ እናት ያለምንም ኢኮኖሚያዊ ጫና ልትተገብረው የምትችለው ተግባር መሆኑን ነው ዶክተር ሄኖክ ዘውዱ የተናገሩት።
በኢትዮጵያ ተለያዩ ተቋማት የሚሰሩ ወላድ እናቶች ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደው ልጅ እነዲያሳድጉ እና ጡት ማጥባት እንዲችሉ 45 ቀን ይሰጥ የነበረውን የወሊድ ፈቃድ ወደ 4 ወራት ከፍ እንዲል መደረጉ የሚታወስ ነው።
በጌትነት ተስፋማርያም