ማይክሮሶፍት ዋጋውን 4.01 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር ሀብት በማስመዝገብ ሁለተኛው የአሜሪካ ኩባንያ ሆኗል።
ከያዝነው የፈንጆች ዓመት 2025 መጀመሪያ ጀምሮ የነበረው የኩባንያው የድርሻ ሽያጭ፤ ከሌላው ጊዜ 28 በመቶ ገደማ መጨመሩን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።
ማይክሮሶፍት እዚህ ወሳኝ ደረጃ ላይ የደረሰው ሀብቱ 3 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር መሆኑን ካሳወቀ ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ነው።
ኩባንያው ለመጀመሪያ ጊዜ ዋጋው 1 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር መድረሱን ያስመዘገበው በሚያዝያ 2019 ሲሆን፣ 4 ትሪሊዮን ዶላር ለመድረስ ስድስት ዓመታት ብቻ ወስዶበታል።
በዚህም የ4.43 ትሪሊዮን ዋጋ ያለውን እና የግራፊክስ ሶፍትዌር አቅራቢ ኩባንያ የሆነውን ኒቪዲያን በመከተል ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
የዎል ስትሪት ተንታኞች እንደጠቀሱት ለማይክሮሶፍት ሽያጭ ከፍ ማለት ‘ኮፓይሎት’ ሰው ሠራሽ አስተውሎት እና ‘አዙር(Azure)’ የክላውድ ሶፍትዌር ምክንያት እንደሆኑ ሲኤንኤን ዘግቧል።
በለሚ ታደሰ