በሶማሌ ክልል ከግንቦት 2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን 340 በላይ ሺህ ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ማከናወናቸውን በክልሉ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም አስታወቀ።
በብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የምስራቅ ሪጅን የጅግጅጋ አካባቢ የምዝገባ አስተባባሪ አቶ ጌዲዮን ጌታቸው እንደገለጹት፤ በክልሉ ከተመዘገቡት ውስጥ 180 ሺህ የሚሆኑት ከጅግጅጋ ከተማ ውጭ ባሉ ወረዳዎችና ዞኖች የተከናወኑ ናቸው።
በክልሉ እሰከ ሰኔ 2018 ዓ.ም ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ለመመዝገብ መታቀዱን ጠቁመው፤ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ወራት ብቻም ከ160 ሺህ በላይ ዜጎች መመዝባቸውን ነው የተናገሩት።
በክልሉ ባሉት ዞኖቾና በ66 ወረዳዎች በትምህርት ቤቶች፣ በዩኒቨርሲቲዎች በባንኮች በንግድ ማዕከላት እንዲሁም በሌሎች የመንግሥት ተቋማት ምዝገባው በመካሄድ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ህብረተሠቡ ከምዝገባው በኋላ ከኢትዮ-ቴሌኮምና እውቅና በላቸው ተቋማት ዲጂታል መታወቂያን በመውሰድ በጥንቃቄ መጠቀም እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በክልሉ የፕሮግራሙን ተደራሽነት በማስፋት ተጨማሪ የምዝገባ ማዕከላትን ለመጨመር የሚያስፈልገው የሰው ኃይል የማሰማራትና የአቅም ግንባታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውንም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በዚህም በክልሉ የህብረተሰቡን የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ፣ በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታው ተሳትፏቸውን ለማረጋገጥ አደረጃጀቶችን በመጠቀም እየተሰራ መሆኑንም አቶ ጌዲዮን አስታውቀዋል።