የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከመገናኛ ብዙኃን እና ከኮሙኒኬሽን ኃላፊዎችና ከፍተኛ ባለሞያዎች ጋር በቅድመ ምክክር ዝግጅት ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነ፣ ምክክሩ አካታችና ስኬታማ እንዲሆን መገናኛ ብዙኃን ለሰላም እና ለአንድነት በመስራ ወሳኝ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
አቶ እውነቱ እንዳስታወቁት፣ ሀገራዊ ምክክሩ የሁሉንም ማኅበረሰብ ክፍሎች ለማሳተፍ ሲባል በቂ ጊዜ የወሰደ ሲሆን፤ ሂደቱን ለማሳካት ሚዲያው የሁሉንም ድምጽ የማድረስ፣ ሐሰተኛ መረጃዎችንና ጥርጣሬዎችን የማጥራት እንዲሁም ትክክለኛውን ትርክት በመፍጠር ለሀገር ሰላም እና አንድነት በጋራ የመሥራት ኃላፊነት አለበት።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር በበኩላቸው፣ መገናኛ ብዙኃኑ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ከኮሚሽኑ ጋር ተባብረው ሊሠሩ እንደሚገባ የጠየቁ ሲሆን፣ መንግሥት ያለምንም ጣልቃ ገብነት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑንና የምክክሩንም ውጤት ለመቀበል ቃል መግባቱን ጠቅሰዋል።
ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም ኮሚሽኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተቋም መሆኑን ገልጸው፣ ምክክሩ ሀገርን የምናሻግርበት ምትክ የሌለው ሂደት በመሆኑ ሁሉም ይህንን ወርቃማ ዕድል ሊጠቀምበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ደግሞ የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚከላከሉ፣ ሥነ ምግባርን የጠበቁና ሕዝቡን ለቅድመ ምክክሩ የሚያዘጋጁ የሚዲያ ሥራዎች ላይ እንዲያተኩር አሳስበው፣ በማንኛውም አስቸጋሪ ወቅት አብረው ለነበሩ መገናኛ ብዙኃን ምስጋና አቅርበዋል።
በመድረኩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ዮሐንስ ሽፈራው (ዶ/ር) እንዳስገነዘቡት፣ ታሪካዊ ችግሮቻችንን በኃይል መፍታት ስላልቻልን አሁን የተገኘውን የምክክር ዕድል መጠቀም ያስፈልጋል።
ሚዲያው ገለልተኛና ከጫና ነጻ የሆነ የተጣራ መረጃ ለኅብረተሰቡ ማድረስ እንዳለበት የጠቆሙት ዶ/ር ዮሐንስ፣ ምክክር ሀሳብ የሚያሸንፍበት የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት እንጂ የሰዎች ውድድር አለመሆኑን ተገንዝቦ ሚዲያው ትክክለኛ ግንዛቤ መፍጠር እንዳለበት አብራርተዋል።