የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ከወንዝ ዳር ልማት ጋር በማስተሳሰር መጪውን ትውልድ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ለመተግበር እየተሠራ መሆኑን የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ አስታወቁ።
በሐረሪ ክልል የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ከወንዝ ዳር ልማት ጋር በማስተሳሰር መጪውን ትውልድ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሠራ ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
በክልሉ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብርን ለማሳካት እየተከናወኑ የሚገኙ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ተዘዋውረው የተመለከቱ ሲሆን፣ ከምልከታው በኋላም በክልሉ ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ የፍራፍሬና የደን ችግኞች ለተከላ ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም ዘንድሮ የሚተከሉ ችግኞች በአረንጓዴ ልማት ረገድ ካላቸው ጠቀሜታ ባለፈ በምግብ ራስን ለመቻል ለሚደረገው ጥረት ከፍተኛ እገዛ የሚያደርጉ፣ ለምግብነትና ለእንስሳት መኖነት የሚውሉ መሆናቸውን ጠቁመው፣ መርሐ-ግብሩን ከወንዝ ዳር ልማት ጋር በማጣመር የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አብራርተዋል።