Search

በቀጣይ ዓመት ዱባይ የኤሌክትሪክ አየር ታክሲ አገልግሎት ልትጀምር ነው

ረቡዕ ኅዳር 10, 2018 144

ዱባይ የመጀመሪያውን የኤሌክትሪክ የአየር ታክሲ የሙከራ በረራዎችን በተሳካ ሁኔታ አከናውና ማጠናቀቋን ይፋ አድርጋለች፡፡
 
ይህ አዲስ፣ ለአካባቢ ተስማሚ የሆነው የትራንስፖርት ዘዴ ከአብራሪው ጋር አራት መንገደኞችን የመያዝ አቅም ያለው ነው።
 
በሰዓት እስከ 320 ኪሎ ሜትር መብረር ይችላል የተባለው የአየር ታክሲ ባትሪው በአንድ ቻርጅ እስከ 160 ኪሎ ሜትር መጓዝ የሚያስችለው ነው።
 
አስፈላጊው መሠረተ ልማት ከተጠናቀቀና እና የሲቪል አቪዬሽን ፈቃድ ከተገኘ በኋላ በአውሮፓውያኑ 2026 መደበኛ የመንገደኞች አገልግሎት ለመጀመር ታቅዷል።
 
ለዚህም አገልግሎት መሠረት የሚሆነው የመጀመሪያው የአየር ታክሲ ጣቢያ ግንባታ 60 በመቶው የተጠናቀቀ ሲሆን፣ በዓመት እስከ 170 ሺህ መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል።
 
በዱባይ አራት የመጀመሪያ ዋና መስመሮች ታቅደዋል ያለው የኤምሬትስ ዜና ኤጀንሲ በቀጣይም ወደ ሌሎች ከተሞች የማስፋፋት እቅድ እንዳለ ተገልጿል።

 

በሰለሞን ገዳ