Search

የባሕር በር፤ የትውልዱ የማይታጠፍ ጥያቄ

ዓርብ የካቲት 20, 2018 53

ዓለም ላይ የባሕር በር ከሌላቸው ሀገራት መካከል በሕዝብ ቁጥሯ ቀዳሚ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ የምታነሳው የባሕር በር ጥያቄ ከሌሎች ሀገራት የሚለየው ቀደም ሲል የነበራትን ታሪካዊ መብት መሠረት ያደረገ በመሆኑ ነው።

ኢትዮጵያ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ራሷ የምታስተዳድረው የባሕር በርና የባሕር ኃይል የነበራት ሀገር እንደነበረች ይታወሳል።

ነገር ግን የሩቅና የቅርብ ጠላቶቿ በጠነሰሱት ሴራ ከባሕር እንድትርቅ መደረጓ፣ ጉዳዩ ለዓመታት እንደ ተዳፈነ እሳት እንዲቆይ አድርጎታል።

የመደመር መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ግን የባሕር በር አጀንዳ እንደ አዲስ የትውልዱ ዋነኛ ጥያቄ ሆኖ ብቅ ብሏል።

ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ ያለ የሕዝብ ቁጥርና ኢኮኖሚ ያላት ሀገር በመሆኗ፣ የራሷ የሆነ የባሕር በር የሚያስፈልጋት ወሳኝ ወቅት ላይ ትገኛለች።

ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለወደብ ኪራይ የምታወጣው በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድረው ጫና ከፍተኛ በመሆኑ፣ የራስን ወደብ መያዝ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ሆኗል።

በአሁኑ ወቅት የቀይ ባሕር ቀጣና ለዓለም ንግድ ልውውጥ ወሳኝ ከመሆኑ ባለፈ፣ ባለው ጂኦፖለቲካዊ አስፈላጊነት በርካታ ሀገራት ዓይናቸውን ጥለውበታል።

ኢትዮጵያም በዚህ ቀጣና ላይ የባሕር በር ባለቤት ለመሆን ሰጥቶ መቀበልን መሠረት ያደረገ ሰላማዊ መንገድን እንደምትከተል በተደጋጋሚ ገልጻለች።

የባሕር በር ባለቤት መሆን የወደብ ኪራይን ከማዳን ባለፈ፣ የወጪና ገቢ ምርቶች በቀጥታ ወደ ዓለም ገበያ እንዲደርሱ በማድረግ ረገድ የላቀ ፋይዳ አለው።

አውሮፓን፣ እስያንና አፍሪካን በሚያገናኘው በዚህ ስልታዊ የቀይ ባሕር ቀጣና ላይ ኢትዮጵያ የራሷ የባሕር በር እንዲኖራት የመደመር መንግሥት ከትውልዱ ጋር በመሆን አስፈላጊውን ዲፕሎማሲያዊና ልማታዊ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።

በሀብተሚካኤል ክፍሉ

#EthiopianBroadcastingCorporation #Ethiopia #RedSea #seaaccess #Geopolitics