ኢትዮጵያን፣ ኤርትራን፣ ሶማሊያን እና ጅቡቲን ያካተተው የአፍሪካ ምሥራቃዊ ክፍል የዓለም ሃያላን ዐይን ያረፈበት ቀጣና ነው። የአፍሪካ ቀንድ ክልላዊ እና ዓለም አቀፋዊ ኃይሎች ትልቅ የስበት ማዕከላቸው አድርገውታል።
ቀደም ሲል ይህን አካባቢ ዋና ትኩረታቸው አድርገው የነበሩት እንደ አሜሪካ እና ቻይና ያሉ “ኃያላን” የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን የአፍሪካ ቀንድ ለአዳዲስ ተወዳዳሪዎች ወሳኝ የፉክክር ሜዳ ሆኗል። ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬትስ፣ ቱርክ፣ ኳታር፣ ኢራን እና ግብፅ በአፍሪካ ቀንድ ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ዋና ቀጣናዊ ተዋናዮች ሆነው ብቅ ብለዋል።
በአሁኑ ጊዜ አሜሪካን፣ ፈረንሳይን፣ ጃፓንን፣ ቻይናን፣ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬትስን እና ቱርክን ጨምሮ አስራ አንድ ሀገራት በቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ የጦር ኃይል ሰፈር አላቸው፣ እዚህ የመገኘታቸው ምክንያት እንደየሀገራቱ ይለያያል፡፡ ይሁንና የቅርብ ጊዜ ጂኦፖለቲካዊ ክስተቶች የአካባቢውን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ በማሳደጉ ቀይ ባሕር ታላቅ የኃይል ሽኩቻ ምሕዋር መሆኑ ግልጽ ነው።
2 ሺህ 250 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የቀይ ባሕር ኮሪደር ሜዲትራኒያን ባሕርን እና ህንድ ውቅያኖስ አልፎ ወደ እስያ የሚገባው ቁልፍ የውኃ መስመር ሲሆን፣ በየዓመቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠር የንግድ እንቅስቀሴ ይከናወንበታል።
ከ10 በመቶ በላይ የሚሆነው የዓለም ንግድ በየዓመቱ በቀይ ባሕር በኩል ያልፋል፡፡ የንግድ መስመሮቹ በዓለም ላይ ካሉት 10 እጅግ ስትራቴጂካዊ የውኃ መንገዶች ሁለቱን ማለትም በባሕሩ ደቡባዊ መግቢያ የሚገኘውን ባብ ኤል-ማንዳብ እና በሰሜን የግብፅ የሚገኘውን ስዊዝ ካናልን ያቋርጣሉ። ይህ የቀይ ባሕር አካባቢ በዘይት እና በከበሩ ማዕድናትም የበለፀገ ነው።
የማሪን ኢንሳይት (Marine Insight) መረጃ እንደሚያመላክተው በቀይ ባሕር ጠረፎች 10 ትላልቅ እና ሥራ የሚበዛባቸው ወደቦች አሉ፡፡ በቀይ ባሕር ዙሪያ ከሚገኙት ሥራ የሚበዛባቸው ወደቦች መካከል የጂዳ ወደብ አንዱ ሲሆን፣ በዓመት ወደ 52 ሚሊዮን ቶን ጭነት፣ 4 ሚሊዮን ኮንቴነሮችን (TEU) እና 275 ሺህ 700 መንገደኞችን ያጓጉዛል።
በፖርት ሱዳን 8.6 ሚሊዮን ቶን ጭነት እና 431 ሺህ ኮንቴነሮች ይጓጓዛል። ሌላው ቀይ ባሕር ላይ የሚገኝ ወደብ የጂቡት ወደብ ሲሆን፣ ከ5.8 ሚሊዮን ቶን በላይ ጭነት እና 293 ሺህ ኮንቴነሮች (TEU) በዓመት ይተላለፍበታል። በምፅዋ ወደብ ደግሞ በዓመት 826 ሺህ ቶን ጭነት ያልፋል።
የሳዑዲ ዓረቢያ ንብረት የሆነው ያንቡ የንግድ ወደብ 1.8 ኪሜ ርዝመት ያለው ሲሆን፣ በዓመት 13.5 ሚሊዮን ቶን ጭነት የሚያስተናግዱ 12 ማረፊያዎች እና 1 ሺህ 500 መንገደኞችን ማስተናገድ የሚችል ልዩ የመንገደኞች ተርሚናል አለው።
የግብፅ ንብረት የሆነው ሳፋጋ ወደብ 100 ሺህ ቶን የመጫን አቅም ያለው የእህል ሲሎ ያለው ሲሆን፣ በዓመት ወደ 742 መርከቦችን በማስተናገድ 3.8 ሚሊዮን ቶን በላይ ጭነት እና ከ876 ሺህ በላይ መንገደኞችን ያስተናግዳል።
የእስራኤሉ ኢላት ወደብ 2.1 ሚሊዮን ቶን ደረቅ ጭነት፣ 70 ሺህ መኪኖችን እና 50 ሺህ ኮንቴነርች በየዓመቱ ያልፉበታል። ሆዴዳ ወደብ የየመን ንብረት ሲሆን፣ 1 ሚሊዮን ቶን የፔትሮሊየም ምርቶችን ጨምሮ 5.7 ሚሊዮን ቶን ጭነት ያስተናግዳል።
አሰብ ወደብ 1.2 ሚሊዮን ቶን ደረቅ ጭነት፣ 32 ሺህ ኮንቴነሮችን (TEU) እና 1.3 ሚሊዮን ቶን ፈሳሽ ጭነት ይተላለፍበት እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ።
ሌላኛው የየመኑ ኤደን ወደብ በዓመት 2 ሺህ መርከቦች የማስተናገድ አቅም ያለው ሲሆን፣ 15.6 ሚሊዮን ቶን ጭነት፣ 380 ሺህ ኮንቴነሮች (TEUs) በዚህ ይተላለፋሉ፡፡
የባሕር በርን የተመለከቱ ዓለም አቀፍ ሕጎች
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የባሕር ሕግ አንቀጽ 69 ንዑስ አንቀጽ 1 እስከ 5 የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በአካባቢያቸው ካለው ባሕር የተፈጥሮ ሀብት እኩል የመጠቀም መብት እንዳላቸው ይደነግጋል፡፡ ይህም፣ ዓሳ ማጥመድን እና በባሕር ውስጥ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን ፍለጋን ጨምሮ ሌሎች ከባሕር ተፈጥሮ ሀብት ጋር የተያያዙ ሀብቶች ተጠቃሚነት መብትን ያካትታል፡፡
የዚሁ ሕግ አንቀጽ 125 ንዑስ አንቀጽ 1 እንደሚያመለክተው ደግሞ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በአካባቢያቸው ያለውን ባሕር የመጠቀም እና የመሸጋገር ዓለም አቀፍ መብት አላቸው። ይህ መብት የባሕር በር በሌለው ሀገር፣ የባሕር በር ባለቤት በሆነው ሀገር እና በቀጣናው መካከል በሚደረግ ስምምነት ሊፈጸም እንደሚገባ በንዑስ አንቀጽ 2 ላይ ተመላክቷል፡፡
አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ ደግሞ እነዚህ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በስምምነት ከተደረገ የተለየ የአገልግሎት ክፍያ ከሌለ በስተቀር ለተገለገሉበት ባሕር ምንም ዓይነት የትራፊክ ታክስ ወይንም ሌላ ክፍያ እንደማይጠየቁ ይደነግጋል፡፡
የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በምስረታ ቻርተሩ መግቢያ ላይ በባሕር ሕግ ጉዳዮች ላይ ባሰፈረው ሀተታ የአፍሪከ ሀገራት የባሕር በር ያላቸውን ጨምሮ ከባሕር ሊያገኙት የሚገባቸውን ጥቅም እያገኙ እንዳልሆነ ጠቅሶ፣ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ከባሕር የመጠቀም መብታቸው ሊጠበቅ እንደሚገባ እና ይህም ከዓለም አቀፍ መርሕ አንጻር ሊታይ እንደሚገባ ይደነግጋል፡፡
ኢትዮጵያ እና የባሕር በር ታሪካዊ ዳራ
የጎን ስፋቱ ከ50 እስከ 60 ኪሎ ሜትር የሚሆነው እና ከመርሳ ፋጡማ ተነስቶ የትግራይን እና አፋርን ምድር እየታከከ ቁልቁል እስከ ራስ ዱሜራስ የሚወርደውን ቀጭን መሬት ያየ ሁሉ፣ የጣሊያን ቅኝ ገዢዎች ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር የሚያስወጣ መሬት እንዳይኖራት ሆን ብለው ያጠሩት አጥር ይመስላል።
ኢትዮጵያ ይህንን አጥር አፍርሳ ኤርትራን ለመቀላለቀል ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ ጥያቄ ባቀረበችበት እና ሙግት ባካሄደችው የዲፕሎማሲ ዘመቻ ወቅት የባሕር በር እንድታገኝ የሚያስችል መሬት ተፈቅዶላት እንደነበረ ያዕቆብ ኃይለማርያም (ዶ/ር) “አሰብ የማን ናት?” በሚለው መጽሐፋቸው ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ የወቅቱ ጥያቄ መላዋን ኤርትራ ከኢትዮጵያ ማዋሃድ ስለነበር ተለይቶ የተሰጣትን የባሕር በር የማግኘት አማራጭ አልተቀበለችውም ነበር።
ክርክሩ እና የዲፕሎማሲው ዘመቻ ፍሬ አፍርቶ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን እንድትቀላቀል ተወስኖ ኢትዮጵያም ዳግም የባሕር ጠረፍ ባለቤት ሆና ነበር።
እንደ ያዕቆብ ኃይለ ማርያም (ዶ/ር) በወቅቱ የነበሩት መንግሥታት በፌዴሬሽኑ አያያዝ ላይ በተከታታይ በፈፀሙአቸው ስህተቶች ፌዴሬሽኑ ፈርሶ በተካሄደው ጦርነት ብዙ ደም ፈሶ ኤርትራ ነጻ ሀገር እንድትሆን በተፈቀደበት ወቅትም ኢትዮጵያ ሕጋዊ የባሕር በር ባለቤትነቷን እንዳታቀርብ በወቅቱ የነበሩት መሪዎቿ ተቃውመው ባዶ እጇን አስቀርተዋታል።
ቀይ ባሕር አካባቢ እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች እና ቀጣይ የአካባቢው እጣ ፈንታ
ከላይ እንደተጠቀሰው አሜሪካ እና ቻይናን ጨምሮ በርካታ ሀገራት በቀይ ባሕር አካባቢ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በትኩረት ከመከታተል አልፎ የጦር ሰፈሮቻቸውን አቋቁመው በአካባቢው ያላቸውን ዓለም አቀፍ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እያፈሰሱ ነው፡፡ እነዚህ ሀገራት አድማስ ተሻግረው እዚህ ሲገኙ ዓለም አቀፍ ሕጎችን በመጥቀስ እና በአካባቢው ያለው ያልተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ በዓለም ላይ ሊፈጥር ይችላል ያሉትን ቀውስ ምክንያት በመስጠት ነው፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግምት መሰረት በቀይ ባሕር ዙሪያ ያለው የሕዝብ ብዛት እ.ኤ.አ 2050 ዓ.ም 343 ሚልዮን ይደርሳል፡፡
የቀጣናው የሕዝብ ቁጥር እያሻቃበ ባለበት በአሁኑ ወቅት አካባቢው ላይ የሚፈጠሩ ቀውሶች ዳፋ ድንበር ተሸሸግሮ አውሮፓ የሚደርስ ነው፡፡ በመሆኑም አውሮፓን ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ከሩቅ ምስራቅ ጋር የሚያገናኘው የቀይ ባሕር እና አንድ ሺህ ኪ.ሜ ርዝመት ያለው የባሕሩ ክፍል ሰላሙ እንዲጠበቅ የአከባቢው ሀገራትን ተሳትፎ ይፈልጋል፡፡
በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ለ24 ዓመታት ያገለገሉት እና በአሁኑ ጊዜ ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የዐረብ ማዕከል (Arab Center Washington DC) ተባባሪ ባልደረባ የሆኑት ቻርለስ ዱኔ እንደሚሉት ቀይ ባሕር ወሳኝ የኢኮኖሚ የደም ቧንቧ ሲሆን፣ ተፈላጊነቱ በመጪዎቹ ዓመታትም ከዚህ በላይ እየጨመረ ሊሄድ ይችላል። በጂኦፖለቲካዊ አገላለጽ፣ ምናልባት ከአሜሪካ እና አውሮፓ ፖሊሲ አውጪዎች ነባራዊ “የመካከለኛው ምሥራቅ” ትኩረት የበለጠ አካታች የፖሊሲ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ሆኖ መታየት አለበት ይላሉ።
በአካባቢው ያለው የአፍሪካ ክፍል በመሠረተ ልማት እጥረት እና በምጣኔ ሀብት ዕድገት ኋላ ቀር ቢሆንም፣ የቀጠናው አቅም እያደገ እና የሕዝብ ቁጥሩ እየጨመረ ሲመጣ በቀይ ባሕር አካባቢ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ ፍላጎት ፣ የትጥቅ ግጭቶች እና የፖለቲካ አለመረጋጋቶች እየሰፋ እንደሚሄድ ተንታኞች ይገልጻሉ።
እነዚህን ዓለም አቀፍ ነባራዊ እና መጻኢ ሁኔታዎችን በመተንተን በቀይ ባሕር አካባቢ የሚያንዣብቡ ሀገራት ግን በአፍሪካ ቀንድ ስትራቴጂያዊ አቀማመጥ ላይ የምትገኘውን እና አካባቢውን አስተሳስሮ ለመያዝ ትልቅ ሚና እየተጫወተች ያለችውን ኢትዮጵያን ይዘነጋሉ፡፡
ከሰባት ዓመታት በፊት በነበረው የሀገሪቱ አመራር ዳተኝነት እና በጉዳዩ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን ማዳፈን የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ወደ ፊት እንዳይመጣ ያደረገ ዋነኛው ምክንያት ነበረ፡፡ ሌሎች ሀገራትም ይህን የኢትዮጵያን መዘናጋት በመጠቀም በአካባቢው ላይ የተለያዩ ጥምረቶችን እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡ ለአብነትም በሳዑዲ ዓረቢያ አስተባባሪነት የተመሰረተው “The Red Sea Forum/Alliance” የሚጠቀስ ነው፡፡
ስምንት ሃገራትን ያቀፈው እና እ.አ.አ በጥር 2020 በሳዑዲ ዓረቢያ አንቀሳቃሽነት የተመሰረተው “The Red Sea Forum/Alliance” ሲቋቋም ኢትዮጵያን እና ሌሎች የጉዳዩን ባለቤቶች ማግለሉ ፍትሐዊ ካለመሆኑም በላይ የጥምረቱን ውጤታማነት ጥርጣሬ ውስጥ ያስገባ እንደሆነም ይገለፃል።
ዛሬ የአትዮጵያ ሕዝብ ከ120 ሚሊዮን በላይ ሲሆን፣ ይህም ኢትዮጵያን በዓለም የባሕር በር ከሌላቸው ሀገሮች ከፍተኛ የሕዘብ ብዛት ያላት ሀገር ያደርጋታል። በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ 17 ሀገሮች የባሕር በር የሌላቸው ሲሆን፣ በእነዚህ ሀገራት ከሚኖረው አጠቃላይ ሕዝብ አንድ ሦሥተኛው የሚገኘው በኢትዮጵያ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ በቀጣይ በአካባቢው ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ቀላል ባለመሆኑ ኢትዮጵያን ያካተተ የጋራ ተጠቃሚነት ላይ መሥራት ምንም ምርጫ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የባሕር በር የምታገኝባቸው ሕጋዊ መሰረቶች
ከላይ የተጠቀሱት ዓለም አቀፍ ሕጎች እና የአፍሪካ ሕብረት ድንጋጌዎች ኢትዮጵያንም የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የአፍሪካ ቀንድ ሲሆን፣ ይህም የጅቡቲ፣ የኤርትራ እና የሶማሊያ የባሕር ዳርቻን ያጠቃልላል። በሱዳን እና በኬንያ በኩል ያለው መስመርም ሌላው የባሕር በርን ለመጠቀም የሚያስችላት አማራጭ መንገድ ነው።
በሌላ አነጋገር የመንሥታቱ ድርጅት በ1982 ባወጣው የባሕር ሕግ አንቀጽ 69 የተጠቀሰው ድንጋጌ፣ ከአንቀጽ 125 እስከ 132 የተገለጹት ድንጋጌዎች እና አንቀጽ 148 የኢትዮጵያን የባሕር መውጫ መብት የሚመለከቱ ናቸው።
በ1900፣ 1902 እና 1908 በኢትዮጵያ እና የኤርትራ ቅኝ ገዢ በነበረችው ጣሊያን መካከል የተደረጉት ስምምነቶች እና የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት በ1964 የቅኝ ግዛት ውሎችን ማጽናቱ ለኢትዮጵያ የባሕር መውጫ መጥፋት ዋና ዋና ምክንያቶች እንደሆኑ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ መምህሩ ዳምጠው ተሰማ “International Law and Ethiopia’s right access to the Sea outlet” በሚለው ጥናታዊ ጽሁፈቸው ጠቅሰዋል፤ ምሁሩ እነዚህ ስምምነቶች ቢኖሩም በሌላኛው ወገን በመጣሳቸው ሕጋዊ ተፈጻሚነት እንደሌላቸው በማስረጃ አስደግፈው አስቀምጠዋል፡፡
ተመራማሪው ስምምነቶቹ ሕጋዊነት የሚያጡባቸውን መሰረቶችም ሲጠቅሱም ጣሊያን እ.አ.አ በ1935 ኢትዮጵያን ዳግም ስትወር የመጀመሪያውን ስምምነት መጣሷን ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ረገድ የቪየና የስምምነት ሕግ አንቀጽ 60 (1) የሁለትዮሽ ውልን በአንደኛው አካል መጣስ ሌላው አካል ለውሉ እንዳይገዛ እና ውሉን የጣሰውን አካል የመክሰስ መብት ይሰጠዋል፡፡
በዚህም መሰረት የ1900፣ 1902 እና የ1908 ስምምነቶች በሌላኛው አካል ስለተጣሰ ተፈጻሚነት እንደሌለው ኢትዮጵያ ተከራክራለች፤ ይህ ደግሞ የአልጀርሱንም ስምምነት ዋጋ ያሳጠዋል፡፡
ሁለተኛ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የ1950ዎቹ ምክረ ሃሳብ እና የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ዳግም በኮንፌዴሬሽን መዋሀድ ‘የኢትዮጵያን የባሕር የማግኘት መብት’ ለመጠየቅ መሰረት ሊሆን የሚችል ስምምነት ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል መምህር ዳምጠው በጥናታዊ ጽሁፋቸው አመልክተዋል፤ እንደዚህ ዓይነቶቹ ተጨባጭ እውነታዎች እና የዓለም አቀፍ የሕግ ድንጋጌዎች የአልጀርሱ ስምምነት ህጋዊ መሰረት እንደገና እንዲገመገም ጥያቄ እንደሚያስነሳ ጠቁመዋል።
ከእነዚህ ሕጋዊ መሰረቶች በመነሳትም
ከአምስት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ሲመጣ በቅድምያ ከተሰሩት ሥራዎች ውስጥ አንዱ የባሕር ኃይል መመስረት ነው። ከፈረንሳይ እስከ ዱባይ ለባሕር ኃይል ሥልጠና ድጋፍ በማፈላለግ የባሕር ኃይልን እንደገና ያደራጀችው ኢትዮጵያ፣ ከ27 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የባሕር ኃይል አድሚራል በመሾም ኃይሉን አጠናክራለች።
ኢትዮጵያ የምታምነው የባሕር በርም ሆነ የቀይ ባሕር ጉዳይ ከኤርትራም፣ ከጂቡቲም፣ ከሶማሊያም፣ ከሱዳንም የገዘፈ የዓለም አቀፍ የጂኦ-ፖለቲካል እና የፖለቲካል ኢኮኖሚ ጉዳይ መሆኑን ነው። የቀይ ባሕር ከሜዲትራኒያን ባሕር እስክ ህንድ ውቅያኖስ ጫፍ፤ ከገልፍ እስከ አፍሪካ ቀንድ ያለውን አካባቢ የሚያካትት ነው። ስለሆነም ጉዳዩ በጥንቃቄ እና በሰጥቶ-መቀበል (Give-and-Take) መርሕ የሚከናውን እንጂ ጦር በመስበቅ የሚደረግ አይደለም።
ያዕቆብ ኃይለማርያም (ዶ/ር) እንደጠቀሱት ኢትዮጵያ የባሕር በር የምታገኝባቸው ነባራዊ ሁኔታዎችም የሚከተሉት ናቸው፡-
F የዓለም አቀፍ ሕጎችን በመጠቀም በቅርቧ የሚገኘውን የባሕር በር የማግኘት መብቷን ማስከበር፣
F ኢትዮጵያ የባሕር በር እንደምትፈልገው ሁሉ የባሕር በር ያላቸው የአካባቢው ሀገራት የእርሻ መሬት አና ሌሎች የሚያስፈልጋቸው ነገሮች ስላሉ እነዚህን በመለዋወጥ ሰጥቶ የመቀበል መርህን ተግባራዊ በማድረግ፣
F ሀገራቱ ወደቦቹን እኩል በማልማት የሚጠቀሙባቸውን ጣምራ ሉዓላዊነት (joint sovereignty) በመፍጠር በጋራ መጠቀም፣
የሚሉት ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ደጋግመው እንደገለጹት ኢትዮጵያም ከነዚህ የሰጥቶ መቀበል አማራጮች ውጭ የመሄድ ዓላማ የላትም፡፡
በለሚ ታደሰ