ዓመታዊ ገቢዋን ከ1 ቢሊዮን ዶላር ወደ 33 ቢሊዮን ዶላር የቀየረችበት ጥበብ፦ ኢንዶኔዥያ
“የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ባትሪ ለማምረት ዋንኛ ጥሬ እቃ የሆነውን ኒኬል ትፈልጋላችሁ? እንግዲያውስ ፋብሪካችሁን ይዛችሁ ኑ!"
ይህ የኢንዶኔዥያ መንግሥት የንግድ ውሳኔ የዓለማችን ቁጥር አንድ የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ አምራች የሆኑትን CATL፣ ቴስላ፣ ሃዩንዳይ፣ BYD፣ ፎርድ የመሳሰሉ አምራቾች ወደ ኢንዶኔዥያ ገብተው ፋብሪካ እንዲከፍቱ ያደረገ በጊዜው አነጋጋሪ የነበረ ውሳኔ ነው።

ዛሬ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት በመመረት ላይ ላሉት የኤሌክትሪክ መኪናዎች የሚያገለግል ባትሪ ለመስራት ያለኒኬል አይታሰብም። ይህ በመሆኑም በአሜሪካ፣ አውሮፓ እና ቻይና የሚገኙ የመኪና አምራች ኢንዱስትሪዎች ህልውናቸው በኒኬል ማዕድን ማግኘት ላይ የተመሰረተ ሆኗል። ይህ በመሆኑም የዚህ ማዕድን ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።
የገበያ ፍላጎቱን ብቻ የተረዱ ኒኬል አምራች ሀገራት ጥሬ ማዕድኑን እያወጡ ወደ ውጭ ሲልኩ ቆይተዋል። የዓለማችንን የኒኬል ማዕድን ውስጥ ከ42% እስከ 52% የሚሆነው ክምችት የያዘችው ኢንዶኔዥያም ከተፈጥሮ ሀብቷ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ እሴት ያልተጨመረበት ጥሬ የኒኬል ማዕድኗን ሲልኩ ከነበሩ ሀገራት መካከል ነበርች።

በተቃራኒው ይህንን ማዕድን ወስደው ለኤሌትሪክ መኪናዎቻቸው ኢንደስትሪ የሚጠቀሙ ሀገራት ደግሞ ይህንኑ ማዕድን አቀናብረው በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ትርፍ ያገኙ ነበር።
በአውሮፓውያኑ 2020 ላይ ግን ኢንዶኔዥያ “ከሞኝ ደጃፍ......” ይሉት ብሂል ይቅርብኝ አለች። የዓለማችን ትልቋ የኒኬል አምራች ሀገር ሆና በዓመት ከ1 ቢሊየን ዶላር የማይበልጥ ገቢ ስታገኝ የቆየችበትን ሁኔታ የሚለውጥ አዲስ የንግድ ህግ በማውጣት የጥሬ ኒኬል ሽያጭን በይፋ አገደች።
ይህ አዲስ ህግ ኢንዶኔዥያ ከእንግዲህ ጥሬ የኒኬል ማዕድን ምርት ወደ ውጭ እንዳይላክና ማዕድኑን የሚፈልጉ ኩባንያዎች በሀገሯ መጥተው ፋብሪካ በመትከል ብቻ በማዕድኑ መጠቀም እንደሚችሉ የሚደነግግም ጭምር ነበር።

ኢንዶኔዥያ ይህንን ህግ ማውጣቷን ተከትሎ ከተለያዩ ሀገራት ተቃውሞ ገጠማት። እርግጥ ማዕድኑ የሚያስፈልጋቸው አሉ። እርሷም ብትሆን ቀላል የማይባል ገቢ ታገኝበታለች። ነገር ግን ሃብቷን እና የዓለመን ፍላጎት ያጠናችው ኢንዶኔዥያ የምታገኘው ገቢ ምንም እንዳልሆነ ተረድታለች።
ዓለም አቀፍ ጫናው በርትቶም የአውሮፓ ህብረት ይህንን የኢንዶኔዥያ የጥሬ ማዕድን ክልከላን በመቃወም በዓለም ንግድ ድርጅት ክስ እንዲመሰረትባት አደረገ። ኢንዶኔዥያ በበኩሏ ከተፈጥሮ ሀብቷ በተገቢው መልኩ የመጠቀም መብት እንዳላት በመግለፅ የኒኬል ማዕድን በጥሬው ያለመሸጥ ውሳኔዋን በማፅናት በሯን ዘጋች።
ከዚህ በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ፍላጎት መናሩን ተከትሎ ይህን ጥሬ እቃ የሚፈልጉት ሀገራትና የኤሌትሪክ ባትሪ አምራች ካምፓኒዎች ጭንቀት ውስጥ ገቡ።

በኢንዶኔዥያ ላይ የተነሳው ተቃውሞ በሀገር ቤትም ጫና እንዲበረታ ቢደረግም በዓለም ላይ በመኪና እጥረቱ ምክንያት ከተፈጠረው ቀውስ የሚበልጥ አልሆነምና ለኢንዶኔዥያ አዲስ ህግ መገዛት ግዴታ መሆኑን እየታየ መጣ።
በዚህም መሰረት ብዙም ሳይቆይ የዓለማችን ግዙፉ የኤሌትሪክ መኪና ባትሪ አምራች የሆነው የቻይናው CATL ወደ ኢንዶኔዥያ በመግባት ቢሊዮን ዶላሮችን ኢንቨስት በማድረግ ግዙፍ የኒኬል ማቅለጫና የባትሪ ማምረቻ ፋብሪካ ተከለ።
በእርግጥ CATL ወደ ኢንዶኔዥያ የመግባት ፍላጎት ቢኖረውም ኢንዶኔዥያም የበረታባትን የሀገራት እና የሀገር ቤት ተቃውሞ ለማርገብ ይህን ድርጅት ወደሀገሯ ለማስገባት ብዙ ጥበብን ተጠቅማለች።
ይህ ጥበቧ ፍሬ አፍርቶ ታዋቂው የአሜሪካ ተሽከርካሪ አምራች ፎርድ ከአንድ የኢንዶኔዥያ ካምፓኒ ጋር በመሆን ኒኬልን በሀገር ውስጥ ለማምረት ተስማማ። የደቡብ ኮሪያዎቹ ሃዩንዳይ እና LG ኢነርጂ ሶሉሽን በጋራ በመሆን በደቡብ ምስራቅ እስያ የመጀመሪያውን የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ ፋብሪካ ገነቡ።

እንዲሁም የዓለማችን ግዙፋ የኤሌክትሪክ መኪኖች አምራች የሆነው ቴስላ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የተቀነባበረ የኒኬል ምርት ለመግዛት ኮንትራት ፈረመ። እናም ኢንዶኒዥያ ሄዶ ኒኬል ምርት ላይ አለመሰማራት ከዓለም ገበያ መውጣት እንደሆነ የገባቸው ሁሉ በብዙ ልመና የሚፈልጓት ሆነች ኢንዶኔዥያ።
ለዓመታት ከኒኬል ማዕድን ሽያጭ በዓመት ከ1 ቢሊየን ዶላር በላይ ሳታገኝ የቆየችው ኢንዶኔዥያ ጥሬ የኒኬል ማዕድን ሽያጭ በማቆም ፋብሪካዎች በሀገሯ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚያስገድደውን ህግ ካወጣች በኋላ ከኒኬል ማዕድን ዘርፍ የምታገኘው ገቢ ከ33 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል። እንዲሁም በሺህዎች ለሚቆጠሩ ዜጎቿ የሥራ እድል መፍጠር ችላለች።
በ2023 በተደረገው የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ (USGS) ግምት መሠረት ኢንዶኔዥያ 55 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የሚሆን የተረጋገጠ የኒኬል ክምችት አላት።
በዋሲሁን ተስፋዬ