Search

የጂኦግራፊ ወጥመድ ይበጠሳል

ሓሙስ ሚያዝያ 22, 2018 112

የዘመናዊው ዓለም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ትርክት የሚጻፈው በመልክዓ-ምድር ብዕር ነው። መልክዓ-ምድር ለአንድ ሀገር የዕድገት መሰላል፣ አሊያም የቁልቁለት ገደል ሊሆን ይችላል።
 
ዛሬ ላይ የብስ እስረኝነት(Landlockedness) ወይም የባሕር በር አልባ መሆን፣ ሉዓላዊነትን የሚያኮስምና ኢኮኖሚን የሚያቀጭጭ ጨካኝ የጂኦግራፊ እስር ቤት ሆኗል። 

በአሁኑ ወቅት በዓለማችን 44 የባሕር በር አልባ ሀገራት ቢኖሩም፣ የዕድገት ደረጃቸውና የጎረቤቶቻቸው ሁኔታ ዕጣ ፈንታቸውን ይወስነዋል። 

እንደ ስዊዘርላንድ ያሉ የአውሮፓ ሀገራት በተቀናጀ የኢኮኖሚ ሥርዓት ውስጥ በመሆናቸው መልክዓ-ምድራዊ ጉዳታቸውን ማቃለል ቢችሉም፤ በእስያ፣ በደቡብ አሜሪካና በአፍሪካ የሚገኙ 32 ታዳጊ የመሬት ዝግ ሀገራት (LLDCs) ግን አሁንም በጎረቤት ሀገራት የጥገኝነት ቀንበር ሥር ይገኛሉ። 

እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ በቅርብ ዓመታት በተፈጸመ ፖለቲካዊ ሸፍጥ ምክንያት ከጥንት ጀምሮ ከኖርንበት ባሕር ተገፍተን የዚህ መሪር ጽዋ ቀዳሚ ተቋዳሾች ሆነናል።

ይህ የጂኦግራፊ እስር ቤት የሚጭንብን የመልክዓ-ምድር ቅጣት (Geographic Penalty) በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም። እነዚህ 32 ታዳጊ ሀገራት የዓለምን 7 በመቶ ሕዝብ ቢይዙም፣ ለዓለም አቀፍ ጠቅላላ ምርት (GDP) የሚያበረክቱት ድርሻ ግን 1 በመቶ ብቻ ነው። 

የነፍስ ወከፍ ገቢያቸውም የባሕር ጠረፍ ካላቸው ሀገራት በ20 በመቶ ያንሳል። ለምን? ምክንያቱም የሎጂስቲክስና የትራንዚት ወጪያቸው አንገት አስደፊ ነው። 

አንድን የንግድ ኮንቴይነር ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የባሕር ጠረፍ ያላት ሀገር በአማካይ 1 ሺህ 434 ዶላር ስታወጣ፣ የባሕር በር አልባ ሀገር ግን 3 ሺህ 884 ዶላር ትከፍላለች። 

ይህ የ63 በመቶ የትራንዚት ወጪ ብልጫ፣ የማምረቻ ዘርፉን የሚያሽመደምድ፣ የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነትን የሚገድልና ሀገራትን በጥሬ ዕቃ ላኪነት ብቻ እንዲወሰኑ የሚያደርግ መዋቅራዊ ማነቆ ነው።

ይህ አሃዛዊ እውነታ ወደ ሀገራችን ሲመጣ ደግሞ ቁጭቱ ልብ ይሰብራል። ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት፣ በቀንድ አፍሪካ የሰላምና የደኅንነት ዋልታ የሆነችው ግዙፏ ኢትዮጵያ የባሕር በር አልባ መሆኗ፣ ከ1985 ዓ.ም ወዲህ የተፈጠረ ስትራቴጂካዊ ስብራት ነው። 

ዛሬ ላይ ኢኮኖሚያችን ከ95 በመቶ በላይ በአንድ የጅቡቲ ወደብ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ነው። የዚህ ጥገኝነት ዋጋ ደግሞ እጅግ ዘግናኝ ነው፤ በየዓመቱ እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር ለወደብ ኪራይ ብቻ ይፈሳል። 

በየዕለቱ 5 ሚሊዮን ዶላር ለትራንዚት እንከፍላለን። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት እንዳስታወሱት፤ ለወደብ ኪራይ የምናወጣው ገንዘብ በየሦስት ዓመቱ አንድ ታላቅ የሕዳሴ ግድብ መገንባት የሚያስችል ግዙፍ ሀብት ነው።
 
ይህ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ኪሳራ የመንግሥት ወጪ ብቻ አይደለም፤ በቀጥታ የዜጎችን ጓዳ የሚያራቁት መሪር እውነታ ነው። 

ማዳበሪያ፣ መድኃኒትና ነዳጅ በውድ ዋጋና በዘገየ የሎጂስቲክስ ሰንሰለት ሲገቡ፣ የኑሮ ውድነቱ ይንራል፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን የሚመረቱ ምርቶች ተወዳዳሪነታቸውን ያጣሉ፣ ወጣቱ የሥራ ዕድል ያጣል፣ የድህነትና የምግብ ዋስትና እጦት ይስፋፋል። ከባሕር የራቀ ኢኮኖሚ፣ ከብልጽግናም የራቀ ነው።

ከኢኮኖሚ ኪሳራው ባሻገር፣ ብሔራዊ ደኅንነታችንና የጂኦ-ፖለቲካዊ ተጽዕኗችን ጥያቄ ውስጥ ወድቋል። በቀይ ባሕር ዙሪያ የባሕር ላይ ወንበዴነትና የጦር መሣሪያ ዝውውር ሲስፋፋ፣ ኢትዮጵያ ይህንን ለመከላከል የሚያስችል የባሕር ኃይልና የባሕር በር ማጣቷ ለስትራቴጂካዊ ተጋላጭነት ዳርጓታል። 

ሀገራችን "የቀይ ባሕር ምክር ቤት" ከመሳሰሉ ቀጣናዊ ስብስቦች "የባሕር ጠረፍ የላትም" በሚል ሰበብ መገለሏ፣ ዲፕሎማሲያዊ ክብዷን የማይመጥን ኢ-ፍትሐዊነት ነው።
ሆኖም፣ ይህንን የጥገኝነት ታሪክ ለመቀየር አሁን ጊዜው ነው።

 ዓለም አቀፍ ሕጎች ከጎናችን ናቸው። በዓለም የንግድ ድርጅት (WTO) የንግድ ማሳለጫ ስምምነቶች፣ በተባበሩት መንግሥታት የባሕር ሕግ ኮንቬንሽን (UNCLOS)፣ እንዲሁም በጥር 2026 ሥራ ላይ በዋለው የ"BBNJ" ስምምነት (High Seas Treaty) መሠረት፣ ባሕር በር የሌላቸው ሀገራት የባሕር ሀብትን የመጠቀምና ወደ ባሕር የመድረስ ጥብቅ ሕጋዊ መብት አላቸው።

ኢትዮጵያ ይህንን "የጂኦግራፊ እስር ቤት" ሰብራ ለመውጣት ቆርጣ ተነስታለች። የባሕር በር ጥያቄ የፖለቲካ ቅንጦት ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ ነው። የምንበላው እህል፣ የምንጠጣው መድኃኒት፣ የልጆቻችን የሥራ ዕድልና የሀገራችን ብሔራዊ ክብር ከዚህ የባሕር በር መከፈት ጋር የተቆራኘ ነው። 

ወደነበርንበት ባሕር ከተጠጋን የምናውቀውን ማዕበል ቀዝፈን ሀገራዊ ብልጽግናችንን እናፋጥናለን፤ በጂኦግራፊያዊ እስር ቤት ውስጥ ታግተን ለመኖር ከወሰንን ግን የጥገኝነት ዕዳ እየከፈልን እንኖራለን። 

ስለዚህ፣ የባሕር በር ጥያቄያችንን ከዳር ለማድረስ እንደ አንድ ልብ አሳቢ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነን በጋራ መቆም ታሪካዊ ግዴታችን ነው። 

አዲሲቷ የተስፋ አድማስ ኢትዮጵያ፣ የጂኦግራፊ ማነቆዋን በጥበብና በጽናት ሰብራ፣ የብልጽግና ደጃፏን በቅርቡ እንደምትከፍት አንጠራጠርም። 

ማነቆው ይሰበራል፤ ኢትዮጵያም በልጆቿ አንድነት ወደ ትክክለኛ ታሪካዊ ልዕልናዋ ትመለሳለች!

 

በአዶኒስ ወ/አረጋይ