Search

የአፍሪካ ስኬት ሁለቱ ምሰሶዎች ሕገ-መንግሥታዊነት እና ውጤታማ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ናቸው - ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ

ዓርብ ኅዳር 19, 2018 76

አፍሪካ ለረጅም ጊዜ ስትፈልገው የነበረውን ውህደት፣ ሰላም እና ብልጽግናን ልታሳካ የምትችልባቸው ሁለቱ ዋና ዋና ምሰሶዎች ሕገ-መንግሥታዊነት እና ውጤታማ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ናቸው ሲሉ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ።

4ኛው የአፍሪካ ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶች ሲምፖዚየምሕገ-መንግሥታዊነት እና ሀገር ግንባታ በአፍሪካበሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ተጀምሯል።

ሲምፖዚየሙ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፣ የዘንድሮው መሪ ቃል የአፍሪካ የዘመናት የፖለቲካ ለውጥ፣ የመልካም አስተዳደር የጋራ ፍላጎት እና የሕዝባችን ዘላቂ የሰላም፣ የፍትሕ እና የብልጽግና መሻትን ማዕከል ያደረገ ነው ብለዋል።

በጉባኤው ላይ ንግግር እንዲያደርጉ ግብዣ ሲደርሳቸው እንደ ጥንታዊቷ ሀገር ፕሬዝዳንት ብቻም ሳይሆን የኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን አካል እንደነበረ ሰው ልምዳቸውን ለማካፈል ግብዣውን በደስታ መቀበላቸውን ጠቁመዋል።

የሕገ-መንግሥታዊነት ፀንሰ ሐሳብ ሕጎችን ስለማውጣት ብቻ ሳይሆን የሕግ የበላይነትን ስለማስፈን፣ ተጠያቂነትን ማፅናት እና መሠረታዊ መብቶችን ማክበር ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ሥልጣን በሕግ ገደብ ውስጥ ተግባራዊ መሆን እንዳለበት የምንረዳበት የሞራል ግዴታ እና መርሕም ጭምር እንደሆነ አንሥተዋል።

ሕገ¬-መንግሥታዊነት አንድን በዘፈቀደ የወጣ ሕግ መከተል ወይም አንድ ዘላቂ ተቋም መገንባት ብቻ አይደለም ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ መንግሥታት ሕጋዊነታቸውን ከሕዝባቸው ፈቃድ ወይም ይሁንታ የሚያገኙት የሐሳቦች ትክክለኛ አምሳያ መሆኑን አንሥተዋል።

ፕሬዚዳንቱ እንዳብራሩት፣ በሀገር ግንባታ ውስጥ መሠረት ከማስቀመጥ አንፃር ሲታይ፣ ሕገ መንግሥት የፖለቲካ ሥልጣንን በመመደብ፣ የመንግሥት ሥልጣን እንዴት እንደሚተገበር ማዕቀፍ በማስቀመጥ እና በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል ማኅበራዊ ውል በመፍጠር ረገድ ያገለግላል፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ እና ሰብአዊ መብቶች ያረጋግጣል።

ከዚህ አኳያ ታዲያ የአፍሪካ የሕገ መንግሥታዊ አስተዳደር ጉዞ ሲታይ ተግዳሮት የበዛበት እና ከጅማሮው በፈተናዎች የተሞላ ነው።

በአህጉሪቱ የሀገረ መንግሥት ግንባታ የተጀመረበት መንገድ ለሕገ-መንግሥታዊነት መሠረት የሆነው የሕዝብ ፈቃድን የተከተለ አልነበረም ነው ያሉት።

ስለዚህ፣ አፍሪካ ውስጥ ሕገ መንግሥታዊ ሐሳቦችን ወደ ዘላቂ አሠራር የመተርጎም ችግር የሚመነጨው በሕገ-መንግሥታዊነት እና በሀገር ግንባታ መካከል ካለው ውስብስብ ትሥሥር እንደሆነ አስረድተዋል።

ይሁን እንጂ አህጉሪቱ ከሕገ-መንግሥታዊነት ጋር በተያያዘ የተፈጠረባት ችግር ተስፋ አስቆራጭ እና የማይለወጥ ታሪክ ሆኖ አለመቅረቱን ጠቁመዋል።

ለዚህ ነፀብራቁ ደግሞ ነፃ አገሮችን ከወለዱ የነፃነት ትግሎች እስከ በቅርብ ጊዜ አስተዳደር የቀረጸው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ድረስ አህጉሪቱ ለነፃነት፣ ለክብር እና ለተጠያቂ አመራር ዘላቂ ፍላጎትን በተከታታይ ማሳየቷ ነው ብለዋል።

ይህ ሁሉ ሲሆን ታዲያ መንገዳችን አልጋ በአልጋ አልነበረም ያሉት ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ደካማ ሕገ መንግሥቶች፣ ተደጋጋሚ ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻዎች እንዲሁም በሚያሳዝን ሁኔታ ሕገ-መንግሥታዊ ያልሆነ ሥልጣን መያዝን የመሳሰሉ ፈተናዎችን መጋፈጥ ቀጥለናል ሲሉ ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንቱ ሕገ-መንግሥታዊነትን በተመለከተ የኢትዮጵያን ተሞክሮ ሲያነሡ፣ በሕገ መንግሥታዊ ልምምድ ረገድ ሀገሪቱ በአንፃሩ ልዩ የሆነ ታሪክ እንዳላት ነው የተናገሩት።

ዘመናትን የተሻገረው ፍትሐ ነገሥት እና ገዳ ሥርዓት ያሉ ሀገር በቀል የሕግ ሥርዓቶች እንዲሁም 20ኛው ክፍለ ዘመን የተጀመሩ ዘመናዊ ሕገ-መንግሥቶች ኢትዮጵያን በተለየ መልኩ የሚገልጿት እንደሆኑ አንሥተዋል።

አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ-መንግሥትም የሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥበቃን ያረጋገጠ እና ከፍ ያደረገ፤ ለብሔሮች እና ብሔረሰቦች መብት እውቅና የሰጠ፤ የኢትዮጵያ አንድነት በሕግ የበላይነት ላይ በመመሥረት ያረጋገጠ፤ ልዩነትን ለማስተዳደር፣ ተሳትፎን ለማሳደግ እና አንድነትን ለማጠናከር የሚያስችል ማዕቀፍ ያቀረበ እንደሆነ አብራርተዋል።

በአጠቃላይ ተግዳሮቶች ቢኖሩም፣ ሕገ መንግሥታዊ እሴቶችን ለማፅናት፣ ተቋማትን ለማጠናከር እና ሕገ-መንግሥታዊነት ዘላቂ የአስተዳደር እና የዜግነት ገጽታ እንደሚሆን ማረጋገጫ ለመስጠት መሠረት መጣሉን ጠቁመዋል።

ሕዝቡን በቅንነት እና በፍትሕ ለማገልገል ያለመ ተቋም መገንባት የፈለግነውን ሰላም እና ብልጽግናን ለመጎናፀፍ በመጨረሻም ማየት የምንፈልገውን አፍሪካ እንድናይ ያስችለናል ሲሉ ተናግረዋል።

ይህንን በተሻለ ሁኔታ ለማሳካት ደግሞ ሕገ-መንግሥታችን የሕዝቡን ሕይወት የሚመሩ መሣሪያዎችን መተው እና በዜጎቻችን መካከል በራስ መተማመንን የሚፈጥር መሆን እንዳለበት ነው የገለጹት።

ኅብረቷ የተጠበቀ፣ ሰላማዊ እና የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ እና አጀንዳ 2063 ማሳካት የሚቻለው ተቋማት መሠረታቸውን ፍትሕ ላይ ሲያደርጉ እና መሪዎች በዜጎች ይሁንታ ሲመረጡ ብቻ ነው ሲሉ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ፍትሕ የሰፈነባት፣ የዘላቂ ሰላም ባለቤት የሆነች እና በሕገ-መንግሥት የምትመራ አፍሪካን ለመንባት ሁላችንም እንረባረብ ሲሉ ፕሬዚዳንት ታየ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በዮናስ በድሉ

#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #Africa #Constitutionalism