Search

ዲጂታል ኢትዮጵያ - ከቴክኖሎጂ ባሻገር ለምን የሕግ ማዕቀፍ ያስፈልገናል?

ማክሰኞ ጥር 19, 2018 112

ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ የምታደርገው ጉዞ በከፍተኛ ፍጥነት እየተጓዘ ነው። ነገር ግን ይህ ጉዞ ስኬታማ እና ተዓማኒ እንዲሆን የሕግ ማዕቀፍ አስፈላጊ ነው። 

ዲጂታል ኢኮኖሚ ስኬታማ እንዲሆን የግል ዳታ ደኅንነት እና ጥበቃ እጅግ አስፈላጊ ሲሆን፤ በዚህ ረገድ በዜጎች ዘንድ መተማመንን መፍጠር ወሳኝ ጉዳይ ነው። 

እያንዳንዱ የሕይወት እንቅስቃሴ ያለ ዲጂታል ቴክኖሎጂ አዳጋች በሆነበት በዚህ ዘመን ኢትዮጵያ ዲጂታላይዜሽኑንም መተማመን የሚፈጥረውን የሕግ ማዕቀፍ ማበጀቱንም ጎን ለጎን እያስኬደች ትገኛለች። 

 ለዚህ ደግሞ እንደ "ዲጂታል መታወቂያ" እና "5 ሚሊዮን ኮደርስ" ያሉ ጅምሮች በጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ መታጀብ እንዳለባቸው በማመን በሕግ ማዕቀፎች ደግፋ የግንዛቤ ሥራዎችን እየሰራችም ትገኛለች። 

ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ - የግል መረጃ ጥበቃ ዋስትና

የዲጂታል መታወቂያ የዜጎችን ማንነት በዘመናዊ መንገድ ለማረጋገጥ መሠረት ነው። ሆኖም ይህ የግል መረጃ በተገቢው ሕግ ካልተጠበቀ ለስጋት ሊጋለጥ ይችላል።

የግል መረጃዎችን (Data Privacy) ጥበቃን በሕግ መወሰን የዜጎችን መተማመን ይፈጥራል። በዚህ ረገድ ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ መኖሩ የዲጂታል መታወቂያው ለባንክ፣ ለጤና እና ለሌሎች አገልግሎቶች በታማኝነት እንዲውል ስለሚያደርግ ኢትዮጵያም ተያያዥ ሕጎችን እና ደንቦችን ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች።

አምስት ሚሊዮን ኮደርስ - የፈጠራና የአጠቃቀም ሥነ-ምግባር

ኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ እያሰለጠነች ነው። ይህ ግዙፍ የሰው ኃይል የዲጂታል ሥነ-ምህዳሩን የሚቀይር ቢሆንም፣ የሕግ ድጋፍ ግን ያስፈልገዋል።

ኮደሮቹ አስተማማኝ የባለቤትነት መብትን (Intellectual Property) ጥበቃ እንዲያገኙ፣ የሳይበር ወንጀልን ለመከላከል እና የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን በሕጋዊ መንገድ ለገበያ ለማቅረብ በሕግ መደገፍ አለባቸው።

ሰልጣኞቹ የሚሰሩት ሶፍትዌር እና መተግበሪያ በሕግ ዕውቅና ሲያገኝ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ተዓማኒ እንዲሆን የሚያስችል ሲሆን፣ ሀገር ደግሞ የጀመረችውን ዲጂታል ኢኮኖሚ እንድታሳካ ይረዳታል። ለዚህም ነው በዚህም ረገድ ሥልጠናውን ከማከናወን ጎን ለጎን የሕግ ማዕቀፉም አብሮ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው። 

የሕግ ማዕቀፍ እንደ "ዲጂታል መሰረተ ልማት"

ዲጂታል መሰረተ ልማት ሲባል ገመድ እና ኢንተርኔት ብቻ አይደለም። "ተዓማኒነት" ትልቁ መሰረቱ ነው። ኢ-ኮሜርስ እና የኦንላይን ግብይትን እንደ ምሳሌ ብንወስድ በዚህ ረገድ የሚሰሩ ስራዎች የሁለንም ወገኖች ተዓማኒነት እንዲያገኙ የዲጂታል ፊርማ እና የውል ሕጎች መኖራቸው ወሳኝ ነው።

በዲጂታል ዓለም ውስጥ "ስህተት ወይም የሕግ ጥሰት ቢፈጠር በምን ሕግ ይጠየቃል?" የሚለው ጥያቄ መመለሱ ለኢንቨስትመንትም ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።

ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ቴክኖሎጂውን መገንባት ብቻውን በቂ አይደለም። የዜጎችን መረጃ የሚጠብቅ፣ ፈጠራን የሚያበረታታ እና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን የሕግ ማዕቀፍ የዲጂታላይዜሽን ጉዞው እስትንፋስ ነው ማለት ይቻላል።

የመደመር መንግሥት የ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂን አውጥቶ ወደ ተግባር የገባው በ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ በቴክኖሎጂ የበለጸገች፣ በሕግ የተጠበቀች እና በዜጎች ዘንድ ተዓማኒ የሆነች ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት ነው። 

በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ጥር 18 ቀን 2018 ዓ.ም ምሽት ኢቲቪ ዜና ላይ የቀረበውን አጀንዳ ይመልከቱ። 

በለሚ ታደሰ