Search

ታላቁ ከበባ፥ የኢትዮጵያ የባሕር መብት እና የግብፅ ያረጀ ስልት

ረቡዕ ታኅሣሥ 22, 2018 772

የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና በውስብስብ ጂኦፖለቲካዊ የለውጥ ሂደት ላይ በሚገኝበት በዚህ ወቅት፤ ግብፅ በሼልፍ ላይ የቆየ ያረጀ፣ ያፈጀ ስልቷን አቧራውን በማራገፍ እንደገና ይዛው መጥታለች።

ሀገሪቱ በቅርቡ ከሶማሊያ እና ከኤርትራ ጋር ፈጸምኩት ያለችው ወታደራዊ ስምምነት፤ በቀጣናው ውጥረትን አንግሷል።

በ“ሉዓላዊነት” እና በ“ቀጣናዊ መረጋጋት” ሽፋን የተፈጸመውን ስምምነት ከታሪካዊ መዛግብት አንፃር ለመረመረው ከጀርባው ያለው ድብቅ ሴራ ፍንትው ብሎ ይታየዋል።

ስምምነቱ በኢትዮጵያ ላይ የተዘጋውን የባሕር በር እስከወዲያኛው በመከርቸም ሀገራችንን ከማዳከም የዘለለ ዓላማ የለውም።

 

👉 የባሕር በር የተዘጋበት ትልቅ ሕዝብ እና ሀገር

በዓለማችን የባሕር በር ከሌላቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ በሕዝብ ቁጥር ትልቋ መሆኗ ይታወቃል። እናም የባሕር በር ለኢትዮጵያ ቅንጦት ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ ነው።

የኢትዮጵያ በመልክዓ ምድር መገለልም እንዲሁ “የታሪክ አጋጣሚ” ተብሎ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም። ይልቁንም ከስምንት አስርት ዓመታት በፊት በዋናነት በግብፅ አቀነባባሪነት ሆነ ተብሎ የተጋረጠባት ስልታዊ መሰናክል ነው።

ግብፅ ይህን ያደረገችው በናይል ተፋሰስ እንዲኖራት ትመኘው ለነበረው የበላይነት “ባለባሕር በሯ ኢትዮጵያ” ስጋት መስላ ስለታየቻት ነበር።

 

👉 የግብፅ የአሻጥር ሌጋሲ

ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ አሻጥር መፈጸሟ በተደጋጋሚ ያጋጠመ እና የተለመደ ነው። ለአብነትም እአአ በ1950ዎቹ ኢትዮጵያ የባሕር በሯን መልሳ በምታገኝበት ሁኔታ ላይ በተመድ ጉባዔ በተደረገበት ወቅት ሀሳቡን ተቃውማ ቆማለች።

በተመሳሳይ፥ በ1960ዎቹ ኢትዮጵያን ለመገንጠል ይዋጉ ለነበሩ ባንዳዎች ምሽግ ሆና ከማገልገል በተጨማሪ የበጀት ምንጫቸው ነበረች።

በ1977ቱ የኢትዮ - ሶማሊያ ጦርነት ወቅት ደግሞ የግብፅ ስልታዊ ከበባ ይበልጥ ይፋ ሆነ። በወቅቱ ግብፅ ለሶማሊያ ወራሪ ኃይል በርካታ የጦር መሳሪያ አስታጥቃለች። ምኞቷም ኢትዮጵያ ስትከፋፈል እንዲሁም ከተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ የባሕር ወሰኗ ስትነጠል ማየት ነበር።

እንሆ ዛሬም ቴአትሩ ቢቀየርም፣ ተዋናዮቹ ያው ሲሆኑ፣ ዓላማቸውም አንድ ነው፤ በኢትዮጵያ ላይ የሚከተሉት የከበባ ፖሊሲ ከስምንት አስርት ዓመታት በኋላ ዛሬም እንደቀጠለ ነው።

 

👉 እውነታው፥ የኢትዮጵያ ብልፅግናን መሻት

ኢትዮጵያ በቅርቡ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት ግልፅ እና ሕጋዊ የኢኮኖሚ ጥያቄ ነው። ግልፅ ፍላጎቷም በዓለም ላይ በጣም ተለዋዋጭ ከሆኑት የባሕር መስመሮች አንዱ በሆነው ቀይ ባሕር ላይ ንግዷን ለማሳለጥ እና ደኅንነቷን ለመጠበቅ የሚያስችላት የባሕር በር ማግኘት ነው።

ግብፅ ይህን የሁለትዮሽ ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ ለማድረግ እና ሶማሊያን ከዓባይ ጋር ለተያያዙ ቅሬታዎቿ እንደ መጫወቻ ካርድ ለመጠቀም ያደረገችው ሙከራ አደገኛ ቁማር ነው። የግብፅ አካሄድ የአፍሪካ ቀንድን የውጭ ኃይሎች የፉክክር ሜዳ በማድረግ ለአሥርት ዓመታት የዘለቀውን የቀጣናዊ ውህደት ጥረት አደጋ ላይ የሚጥልም ነው።

 

👉 ቀጣዩ መንገድ

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሊገነዘበው የሚገባው ጉዳይ፣ ኢትዮጵያ ላይ በር በመዝጋት በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላም ማስፈን እንደማይቻል ነው። ወደብ አልባ በመሆኗ ለከፍተኛ የወደብ ክፍያዎች እና ስትራቴጂያዊ ጥገኝነት የተጋለጠችው ኢትዮጵያ በዚህ ሁኔታ ታፍና ለረጅም ጊዜ መቆየት አትችልም።

ይህን ዑደት ለመስበር የሚያስፈልጉ ሦስት መሰረታዊ ጉዳዮች፡-

ዲፕሎማሲያዊ ግልጽነት፡- የአፍሪካ ሕብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከካይሮ ድርጊት ጀርባ ያሉ መልዕክቶችን ማየት አለባቸው። ቀጣናውን ወደ አለመግባባት እየገፋ የውጭ ጣልቃገብነት የሚስበውን ድርጊት ለማጋለጥ መሥራት ያስፈልጋል።

ቀጣናዊ ትብብር፡- የኢትዮጵያ ጎረቤቶች የበለፀገች እና የባሕር መውጫ ያላት ኢትዮጵያ የቀጣናው ንግድ ሞተር እንጂ የሉዓላዊነት ስጋት እንዳልሆነች መገንዘብ አለባቸው።

ፍትሃዊ የሀብት መጋራት፡- ዓባይ የትብብር ድልድይ እንጂ የባሕር በርን ለመዝጋት ምክንያት መሆን እንደሌለበት ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

ታሪክ እንደሚያሳየው አንድን ሀገር ወደኋላ ለመጎተት የተፈጠሩ ሰንሰለቶች በመጨረሻ መበጠሳቸው አይቀሬ ነው። ኢትዮጵያም በሴራ ወደ ተገለለችበት ቀይ ባሕር መመለሷ አይቀሬ ነው። የኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር መመለስ መልክዓ ምድራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ የሚያመጣ ነው። ብቸኛው ጥያቄ የሚሆነው “ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር የምትመለሰው በቀጣናዊ አጋርነት መንፈስ ነው ወይስ ለመቶ ዓመታት የቆየውን የሴራ ስትራቴጂ ለመስበር?” የሚለው ነው።

በለሚ ታደሰ

#EBCdotstream #HornofAfrica #Ethiopia #RedSea #Egypt 

የእንግሊዝኛ ዘገባው ከስር ተያይዟል:-

https://www.ebc.et/english/Home/NewsDetails?NewsId=3768