ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት ከእንግዲህ ወደኋላ በማይመለስበት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
ብዙዎች የብሪክስ አገራት የጋራ ወረቀት ገንዘብ እስኪያትሙ በጉጉት ሲጠብቁ፣ አገራቱ ግን የዓለምን የኢኮኖሚ ሚዛን የሚቀይር ኃያል ስትራቴጂ ነድፈዋል።
ይህ አዲስ ስልት በወረቀት ገንዘብ ሽኩቻ ውስጥ ከመግባት ይልቅ፣ የቴክኖሎጂውን ልዕልና በመጠቀም የየአገራቱን ማዕከላዊ ባንክ ዲጂታል ገንዘቦች (CBDCs) በማስተሳሰር አይያተኮረ ነው።
ይህ የዲጂታል አብዮት አባል አገራቱ ያለምንም መካከለኛ ባንክ በቀጥታ እንዲገበያዩ የሚያስችል ስለመሆኑ ነው የተዘገበው።
ለምሳሌ በኢትዮጵያና በቻይና መካከል የሚደረግ የንግድ ልውውጥ በዲጂታል ቴክኖሎጂ አማካኝነት በቀጥታ በየአገራቱ ገንዘቦች እንዲፈጸም በር ይከፍታል።
ይህም የግብይት ወጪን ከመቀነሱና ፍጥነትን ከመጨመሩ ባለፈ፣ አገራት ከቁጥጥር ነፃ ሆነው የራሳቸውን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እንዲያስከብሩ ያስችላቸዋል።
ብሪክስ ይህንን አማራጭ የመረጠው ከዚህ ቀደም ህንድና ሩሲያ በራሳቸው ገንዘብ ለመገበያየት ሞክረው ካጋጠማቸው የ"ሩፒ ወጥመድ" ትምህርት በመውሰድ ነው።
አዲሱ የዲጂታል መረብ ገንዘብ በአባል አገራቱ መካከል ያለምንም እንቅፋት እንዲዘዋወር ስለሚያደርግ፣ የፋይናንስ ሥርዓቱን ይበልጥ ፍትሐዊና አስተማማኝ ያደርገዋል።
የብሪክስ አገራት እያከናወኑት ያለው ይህ የቴክኖሎጂ ሽግግር የነገዋን ዓለም ኢኮኖሚያዊ ገጽታ ሙሉ በሙሉ የሚቀይር ታላቅ ኩነት ሆኖ ተመዝግቧል።
በሰለሞን ገዳ