Search

የቀይ ባሕር አፋር በኤርትራ መንግሥት የዘር ማጥፋት እና የመብት ጥሰት እየተፈፀመበት ነው፡- የቀይ ባሕር አፋር ዲሞክራሲያዊ ድርጅት

ረቡዕ ታኅሣሥ 15, 2018 435

የቀይ ባህር አፋር ሕዝብ በኤርትራ መንግሥት መንግሥታዊ የዘር ማጥፋት እና የመብት ጥሰት እየተፈፀመበት ነው ሲል የቀይ ባሕር አፋር ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ገለፀ።
‎ድርጅቱ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፤ የኤርትራ መንግሥት ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ በኤርትራ ደናክል አካባቢ የሚኖሩ የቀይ ባሕር አፋሮች ላይ መንግሥታዊ የዘር ማጥፋት የመብት ጥሰት እየፈፀመ ቆይቷል ብሏል።
‎የድርጅቱ ሊቀመንበር ኢብራሂም ሀሩን በመግለጫው እንደተናገሩት፤ የኤርትራ መንግሥት በአፋሮች ላይ ከሕግና ከፍርድ ውጭ ግድያዎችና ዘር ተኮር ጭፍጨፋ፣ ያለፍርድ ማሰርና ማሰቃየት፣ መሰወር፣ የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ በግዳጅ ማፈናቀል እየፈፀመ መሆኑን ጠቅሰዋል።
‎በቋንቋችን እንዳንማር በመከልከል፣ መስጊዶችን በመዝጋት እና የቁርአን ትምህርትን በመከልከል የቀይ ባሕር አፋር ሕዝብን ባህልና ማንነት በማጥፋት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።
‎ከቀይ ባሕር አሳ ማጥመድ መከልከልን ጨምሮ ኢኮኖሚያዊ መብቶችን በመጣስ የሕልውና አደጋ ውስጥ አስገብቶናል ሲሉም የድርጅቱ ሊቀመንበር ኢብራሂም ሀሩን አስረድተዋል።
‎በዚህ ምክንያት በርካታ የቀይ ባሕር አፋሮች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው እየተሰደዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
‎የኤርትራ መንግሥት ዓላማ የቀይ ባሕር አፋሮችን ከቀይ ባሕር ማስለቀቅ መሆኑንም ሊቀመንበሩ ተናግረዋል።
‎ድርጅቱ የኤርትራ መንግሥት በኤርትራ አፋሮች ላይ እያደረሰ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተመለከተ ክስ ለአፍሪካ የሰብዓዊ እና ሕዝባዊ መብቶች ኮሚሽን ማቅረቡን ገልጿል።
‎ድርጅቱም 122 ገጽ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዝርዝር መረጃ ከነሙሉ ማስረጃው ለአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አስገብቷል።
‎ኮሚሽኑም ጥያቄውን ተቀብሎ መመዝገቡን እና ለጥያቄው ዕውቅና በመስጠት የኤርትራ መንግሥት በ60 ቀን ውስጥ መልስ እንዲሰጥ ክስ መላኩን አሳውቆናል ብለዋል።
‎የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረትና ሌላውም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ትኩረት ሰጥቶት ምርመራ እንዲያደርግ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስዱም ጠይቀዋል።
በባዬ ሙላት