ዛሬ ላይ በዓለማችን እጅግ ሀብታም እና የበለፀጉ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ የምትገኘውን የስዊዘርላንድን የኋላ ታሪክ መለስ ብለን ስናየው፣ በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በአውሮፓ ከፍተኛ ድህነት ከነበረባቸው ሀገራት አንዷ ነበረች።
የድህነት እና የስደት ዘመን
ስዊዘርላንዳውያን "የአውሮፓ ድሆች" ተብለው በሚጠሩበት በዚያ ዘመን፣ ከአስከፊ ድህነት የተነሣ ሕዝቡ የሚበላው አጥቶ በረሃብ ይሰቃይ ነበር።
በዚህም ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በተፈጥሮ ሀብት ያልበለጸገችውን ሀገራቸውን በመተው የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ወደ አሜሪካ፣ እስያ እና ወደ ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ይሰደዱ ነበር።
ከዚህም ባለፈ፣ የሀገሪቱ ወጣቶች ወደተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት በመሰደድ በቅጥር ወታደርነት ሕይወታቸውን ለከባድ አደጋ አጋልጠው በመስጠት ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት ተገድደዋል።
የቫቲካን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የክብር ዘብ (Swiss Guard) የመሆን ታሪክም የመነጨው ከዚሁ የቅጥር ወታደርነት ታሪክ ነው። ዛሬም ድረስ ቫቲካንን የሚጠብቁት የስዊስ ዜጎች መሆናቸው የዚያ ዘመን ታሪክ ቅርስ ነው።
ሌላው ልብ የሚነካው የታሪኩ አካል ‘ኮንትራት ልጆች’ (Verdingkinder) የሚባለው ነው። በወቅቱ ደሃ የሆኑ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን መመገብ ስለማይችሉ፣ ዕድሜያቸው ለሥራ ያልደረሱ ሕፃናትን ለሀብታም ገበሬዎች ያለ ደመወዝ እንዲያገለግሉ አሳልፈው ይሰጡ ነበር።

የለውጥ መጀመሪያ፦ ጦርነት እና ብሔራዊ መግባባት
ስዊዘርላንድ የሕዝቧን አቅም ተጠቅማ እንዳታድግ ካደረጓት ምክንያቶች ዋናው በሀገሪቱ ውስጥ የተንሰራፋው ክልላዊ እሳቤ፣ የእርስ በርስ ግጭት እና በሊበራል እና ወግ አጥባቂ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል የነበረው ልዩነት ነበር።
ይህ ልዩነት እ.አ.አ. በ1847 ወደ "ሶንደርቡንድ" (Sonderbund War) የእርስ በርስ ጦርነት አመራ።
ሆኖም ጦርነቱ ለ27 ቀናት ብቻ እንደቆየ፣ ስዊዘርላንዳውያን ከመከፋፈል እና ከጥፋት ውጭ የሚያተርፉት ነገር እንደሌለ ተረዱ። እጣ ፈንታቸውን በገዛ እጃቸው ለመጻፍ ወሰኑ።
የ1848 ሕገ-መንግሥት፦ በቋንቋ፣ በሃይማኖት እና በባህል ተከፋፍላ የነበረችውን ሀገር ወደ አንድነት ያመጣ እና ዛሬ ላለችው ስዊዘርላንድ መሠረት የጣለውን ሕገ-መንግሥት በ1848 (እ.ኤ.አ) አፀደቁ።
የውይይት ባሕል፦ ልዩነቶችን ወደ ጦርነት ሳይሆን ወደ ሕግ እና ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት በመለወጥ ፖለቲካዊ መረጋጋትን ፈጠሩ።

ስዊዘርላንድ ወደ ብልፅግና ያደረገችው ጉዞ
ፖለቲካዊ መረጋጋት ሲሰፍን፣ ስዊዘርላንዳውያን ትኩረታቸውን ወደ ልማት አዞሩ። የተፈጥሮ ሀብት (ማዕድን) ስለሌላቸውም ትኩረታቸውን በሠለጠነ የሰው ኃይል ላይ አደረጉ፤ በዚህም ወደ ኢንደስትሪ፣ ሰዓት አመራረት እና የባንክ ሥራ በስፋት ተሰማሩ።
በዓለም አቀፍ የፈጠራ ኢንዴክስ (Global Innovation Index) ለተከታታይ ዓመታት አንደኛ ደረጃን በመያዝ የቴክኖሎጂ ማዕከል ሆኑ።
የስዊዘርላንድ ገንዘብ (የስዊስ ፍራንክ) በዓለም ላይ እጅግ አስተማማኝ መገበያያ ሆኗል።
ዛሬ ላይ ስዊዘርላንድ ከአስከፊ ረሃብ እና ስደት ወጥታ፣ የዓለማችን የፋይናንስ ማዕከል እና የሰላም ተምሳሌት መሆን ችላለች።
ይህም የሚያሳየው ብሔራዊ መግባባት እና አንድነት ለአንድ ሀገር ዕድገት ምን ያህል ወሳኝ እንደሆኑ ነው።
በዋሲሁን ተስፋዬ
#EthiopianBroadcastingCorporation #nationaldialogue #Switzerland #ከግጭት_ወደ_ውይይት