Search

ኢትዮጵያ በፈጠራ እና በክህሎት ጉዞ ላይ

ረቡዕ ጥር 20, 2018 33

የዛሬው ዓለም በዕውቀትና በፈጠራ የሚመራ መሆኑን በመረዳት፣ የመደመር መንግሥት የወጣቶችን አቅም ለመገንባትና ሀገሪቱን የቴክኖሎጂ ባለቤት ለማድረግ ሰፋፊ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በዚህ ዘርፍ የታዩት መሠረታዊ ለውጦች፣ ለነገዋ ጠንካራ ኢትዮጵያ ግንባታ ጽኑ መሠረት እየጣሉ መሆኑን ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል።

የአምስት ሚሊዮን ኮደሮች (5M Coders) ኢኒሼቲቭ በክህሎት እና ፈጠራ ረገድ ልዩነት ያመጣል ተብሎ የሚጠበቅ ነው። ወጣቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ የሆነውን የኮዲንግ ክህሎት እንዲጨብጡ በማድረግ፣ በዲጂታሉ ዓለም ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ትልቅ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል።

ስታርት አፕ (Startup) ሌላኛው በቴክኖሎጂ የታገዘ ክህሎት እና ፈጠራን የሚያበረታታ መርሐ ግብር ነው። የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ሰዎች ፈጠራቸውን ወደ ሃብት እንዲቀይሩ የሚያስችሉ አዋጅ እና ድጋፎች ሥራ ላይ ውለዋል። ለስታርታፕ የሚሆን ቦታ እና ሥነ-ምህዳር ተፈጥሮ ወጣቶች ሃሳባቸውን እያበለፀጉ ይገኛሉ።

አዳዲስ የፈጠራ ሐሳብ ያላቸው ወጣቶች ወደ ቢዝነስ እንዲገቡ ለማበረታታት የፖሊሲ ማሻሻያዎች ተደርገዋል። ይህም የፈጠራ ውጤቶች ወደ ገበያ እንዲመጡ እና የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ መንገድ እየከፈተ ይገኛል።

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ለክህሎት እና ፈጠራ ልዩ ቦታ ይሰጣል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ የተቀረጸው ይህ ስትራቴጂ፣ ከመንግሥት አገልግሎት እስከ ግል ዘርፉ ያለውን አሠራር ያዘምናል፤ በፈጠራ የታገዘ ፈጣን አገልግሎትንም እውን ያደርጋል። 

የክህሎት እና የቴክኒክ ሥልጠና ማዕከላት (TVET) ከንድፈ ሃሳብ ያለፈ ተግባራዊ ሥልጠናዎችን እየሰጡ ይገኛሉ። አነዚህ ተቋማት ዘመኑ የሚፈልገውን ክህሎት የታጠቁ ወጣቶችን በማፍራት ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እየተወጡ ነው። ተቋማቱ በፖሊሲ ታግዘው ገበያው የሚፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል የማፍራት ተልዕኮአቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።

በለሚ ታደሰ