Search

በኢትዮጵያና በእስራኤል ትብብር የተዘጋጀ የሳይበር ደኅንነት አውደ ጥናት ተካሄደ

ሓሙስ ጥር 14, 2018 316

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤምባሲ ትብብር የተዘጋጀው "የሳይበር ደኅንነት አዝማሚያዎች እና ዕድገቶች" ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት ተካሄደ፡፡
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሉቀን ቀሬ፣ "የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ራዕይን ለማሳካት በሳይበር ደኅንነት ላይ ሰፊ ልምድና ትልቅ አቅም ከአላት እስራኤል ጋር በትብብር መሥራት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት ትብብር የኢትዮጵያን ዲጂታል ኢኮኖሚ ከማፋጠኑም ባለፈ ለውጭ ኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ እንዲሁም የፋይናንስና ስልታዊ መሠረተ ልማቶችን ከሳይበር ጥቃት የሚከላከል አስተማማኝ የዲጂታል ምኅዳር ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
የሳይበር ጥቃቶችን ለመከላከልና ጠንካራ የቴክኖሎጂ መሰረት ለመገንባት ራስን ማብቃትና ከዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች መማር አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑም ተገልጿል።
በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አቭራሃም ንጉሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የሳይበር ደኅንነት የሀገር ደኅንነት እና የኢኮኖሚ ጥንካሬ መሰረት መሆኑን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞዋ የዲጂታል ሃብቶቿን ይበልጥ መጠበቅ እንዳለባት አመላክተዋል።
እስራኤል ባለፉት ሁለት ዓመታት የሳይበር ምኅዳሩን እንደ ትልቅ የጦር ግንባር በመመልከት በመንግሥትና በግል ዘርፎች ያሏትን የመከላከል አቅም ማጠናከሯን አምባሳደሩ ገልጸዋል።
የእስራኤል የሳይበር ደኅንነት ስኬት በብቁ የሰው ኃይል፣ በተቋማት ትብብርና በፈጠራ ባህል ላይ የተመሰረተ መሆኑን በመጥቀስ፣ ይህን ተሞክሮ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ ለመተግበር ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።
አውደ ጥናቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረውን ታሪካዊ ግንኙነት ወደ ቴክኖሎጂ እና ፈጠራ አዘል ትብብር በማሸጋገር ረገድ አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍትና የኢትዮጵያን ዲጂታል የወደፊት እጣ ፈንታ አስተማማኝ ለማድረግ እንደሚረዳ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።