Search

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተሳካ እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ወሳኝ ነው - ምርጫ ቦርድ

ሰኞ ጥር 25, 2018 80

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊ፣ ገለልተኛ እና የተሳካ እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የባለድርሻ አካላት ሚና ወሳኝ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ ገለፁ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ይገኛል።
በውይይት መድረኩ ላይ ወ/ሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዝግጅቶቹም መካከል ከፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመመካከር የምርጫ የግዜ ሰሌዳ በማውጣት ህዳር 30 ቀን 2018 ለህዝብ ይፋ መደረጉን ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የህግ ማሻሻያ በማስፈለጉ ከ 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ተሞክሮ በመውሰድ የህግ እና የመመሪያ ማሻሻያ ስራ መሰራቱን ጠቅሰዋል።
ዜጎች በእውቀት ለይ የተመሰረተ ምርጫ እንዲያከናውኑ ለማገዝ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶችን በማሳተፍ የመራጮችን ግንዛቤ ሊያሳድጉ የሚችሉ ትምህርቶች እየተሰጡ መሆናቸውን ሰብሳቢዋ ተናግረዋል፡፡
የምርጫ አስፈፃሚዎች ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመመካከር ገለልተኝነታቸውን በማረጋገጥ እንዲሁም በፈተና የታገዘ ልየታ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩዎች ምዝገባ ቦርዱ ባበለፀገው መተግበሪያ አማካኝነት እየተከናወነ መሆኑን የገለፁት ሰብሳቢዋ ፤ የምዝገባ ሂደቱ ቀልጣፋ እንዲሆን ቦርዱ ስልጠና በመስጠት ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
የእጩ ምዝገባ ከተጠናቀቀ በኋላ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፖሊሲዎቻቸውን ለህዝብ ይፋ የሚያደርጉበት የክርክር መድረክ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ ከማን ምን ይጠበቃል የሚሉ ተከታታይ ውይይቶች ከባለድርሻ አካላት ጋር መደረጉን ያስታወሱት ሰብሳቢዋ፤ በዛሬው የውይይት መድረክ ተለዋዋጭ የሆነውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት በየክልሉ ያሉ አስቻይ ሁኔታዎችን ለመገምገም የተዘጋጀ መሆኑን አንስተዋል።
ወ/ሮ ሜላተወርቅ አክለውም፤ ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በውይይት መድረኩ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ የከተማ አስተዳደሮች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በምንተስኖት ይልማ