የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) በአፍሪካ ሚዲያ አዋርድ ልዩ ተሸላሚ ሆኗል።
በሬድዮም ሆነ በቴሌቪዥን ቀዳሚ እና የኢትዮጵያ የበኩር ድምፅ የሆነው ኢቢሲ ላለፉት ዓመታት በዘርፉ ከፍተኛ አበርክቶ ያለው መሆኑ ይታወቃል።
ብሔራዊ ሚዲያው ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካውያን አንድነት፣ ትብብር እና በጋራ መቆም ትልቅ ድርሻ የነበረው ነው።

የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄን በማፋፋም፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሠረት በማገዝ እንዲሁም አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ለመውጣት የነፃነት ትግል እንዲያደርጉ በማነቃነቅ ታሪካዊ ሚናን ተጫውቷል።
በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያ የምታከናውናቸውን የልማት ሥራዎች በዘርፈ ብዙ አማራጮቹ ከማሳለጥ እና ለዓለም ከማስተዋወቅ ባሻገር፣ አፍሪካ የጋራ ልማት እና ተጠቃሚነቷን ታረጋግጥ ዘንድ በአባል ሀገራት መካከል የትብብር መንፈስን ለማጠናከር እየሠራ ይገኛል።

የአፍሪካ መገናኛ ብዙኃን በተለያዩ መንገዶች ለአፍሪካ ዕድገትና ከፍታ እየሠሩ ላለው ሥራ እውቅና ለመስጠት በተካሄደው የአፍሪካ ሚዲያ አዋርድ፤ ኢቢሲ ያበረከተው አስተዋፅዖ ከሌሎች ሚዲያዎች ጋር ተወዳድሮ ልቆ በመገኘቱ ነው ልዩ ተሸላሚ መሆን የቻለው።
በአዲስ አበባ በተካሄደው የሽልማት ሥነ-ሥርዓት በምርጥ ቪድዮ ፕሮዳክሽን ዘርፍ፣ በአፍሪካን ኢንዲፔንደንት ዘርፍ (African Independent Category) እንዲሁም በአፍሪካ የባህል ጥበቃ ዘርፍ (African Cultural Heritage) ለአሸናፊዎች ሽልማት ተበርክቷል።
#EBC #ebcdotstream #AficanMediaAwards