በርካታ አፍሪካውያን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆኑ፣ ለዓለም አቀፍ ችግሮችም መፍትሔ የሚያመነጩ የፈጠራ ባለቤቶች መሆናቸውን በተለያዩ አጋጣሚዎች አሳይተዋል።
የፋይናንስ ቴክኖሎጂው (Fintech) ዘርፍ አፍሪካን ከባህላዊና ቢሮክራሲያዊ የባንክ አሠራር በማላቀቅ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ወደ ዘመናዊ የገንዘብ ሥርዓት ውስጥ እያስገባ ይገኛል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአፍሪካ ስታርት አፖች የሚንቀሳቀሰው ከፍተኛ ኢንቨስትመንት አህጉሪቱ ለዓለም አቀፍ ባለሀብቶች ያላትን ሳቢነት የሚያሳይ ሆኗል።
ይህ የዲጂታል አብዮት የፋይናንስ አካታችነትን ከማረጋገጥ ባለፈ፣ የድንበር ተሻጋሪ ንግድን በማቀላጠፍና ለወጣቱ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ የአንበሳውን ድርሻ እየተወጣ ነው።
በአፍሪካውያን የተሰሩ የፋይናንስ ቴክኖሎጂዎች በአህጉሪቱ የዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸው የአፍሪካ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ ጉባኤ መስራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዘካሪያስ አምሳሉ ይገልጻሉ።
አፍሪካውያን የፈጠራ ባለሙያዎች ያበለፀጓቸው የፋይናንስ ቴክኖሎጂዎች መስፋፋት የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓቱን በማጠናከር፣ አፍሪካ የዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ማዕከል እንድትሆን ከፍተኛ አበርክቶ እንዳለውም አብራርተዋል።
የተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2025 ለአፍሪካ ዲጂታል ዘርፍ እድገት ወሳኝ ዓመት እንደነበር የጠቀሱት ዘካሪያስ አምሳሉ፤ የተጀመሩ የፋይናንስ ቴክኖሎጂዎችም በአፍሪካ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ ትርፋማ ወደሚሆኑበት አቅጣጫ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
አፍሪካውያን የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ከሞባይል ገንዘብ ዝውውር እስከ ክላውድ ኮምፒዩቲንግ የፈጠራ ሥራዎች ላይ በመሰማራት፣ ከአህጉሪቱ አልፈው በዘርፉ ለዓለም እድገት ትልቅ አስተዋፅዖ እያበረከቱ መሆኑንም አስረድተዋል።
በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የፋይናንስ ቴክኖሎጂ ጀማሪዎች ፈቃድ አግኝተው ከባንኮች ጋር በጋራ መሥራት የሚችሉበት አውድ መፈጠሩ የባንኮችን ተደራሽነት ለማሳደግ እንደሚያግዝም ነው የገለጹት።
የአፍሪካ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ እ.ኤ.አ. በ2026 ከፍተኛ እድገት እንደሚያመዘግብ ይጠበቃል ሲሉም ዘካሪያስ አምሳሉ አስረድተዋል።
በላሉ ኢታላ