በታሪክ ውስጥ ታላላቅ ፈጠራዎች የመነጩት በረጅም ጊዜ የምርምር ሥራ ብቻ አይደለም።
አንዳንድ ጊዜ ታላላቅ እና ዓለምን መቀየር የቻሉ ፈጠራዎች እና ግኝቶች የተገኙት በአንድ ቀላል እና ድንገተኛ አጋጣሚም ነው።
ከነዚህም መካከል የዓለምን ግብርና ዘዴ መቀየር ከቻሉ ዘመናዊ የእርሻ ዘዴዎች መካከል አንዱ የሆነው የጠብታ መስኖ (Drip Irrigation) ታሪክ ይገኝበታል።
ዛሬ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ሀገራት እየተጠቀሙበት ያለው የጠብታ መስኖ ዘዴ በአጋጣሚ የተፈጠረው ከአንድ ዛፍ ሥር ውኃ ሲያንጠባጥብ በተገኘ የተበላሸ የውኃ መስመር ምክንያት ነበር።
ይህንን የተበላሸ የውኃ መስመር አይቶ ሐሳቡን ወደ የጠብታ መስኖ (Drip Irrigation) የቀየረው የፈጠራ ሰው ታሪክ እንመልከት፦
የሲምቻ ብላስ የሕይወት እና የፈጠራ ጉዞ
ሲምቻ ብላስ እ.አ.አ በ1897 ዓ.ም በፖላንድ ዋና ከተማ ዋርሶው ተወለደ። የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ዋርሶው በሚገኘው የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በሲቪል ምሕንድስና የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል።
ብላስ በትምህርቱ ወቅትም ሆነ ከዚያ በኋላ በሃይድሮሎጂ እና በውኃ አያያዝ ቴክኖሎጂዎች ላይ የተለያዩ ምርምሮችን ሲሠራ የቆየ ሲሆን፣ ለግብርናው ዘርፍ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረከተውን እና የመጀመሪያ የፈጠራ ሥራው የሆነውን የዘር መትከያ ማሽን (Wheat Planting Machine) መፍጠር የቻለውም በዚህ ጊዜ ውስጥ ነበር።
በወጣትነቱ የተለያዩ ግብርና ነክ ምርምሮችን ሲያካሄድ የቆየው ሲምቻ ብላስ፣ በ1920ዎቹ መጀመሪያ ላይ ወደ ፍልስጤም (በኋላም እስራኤል) በመጓዝ ኑሮውን በዚያ አድርጎ በሙያው መሥራት ጀመረ።
ብዙም ሳይቆይ በ1930ዎቹ የእስራኤል ብሔራዊ የውኃ ኩባንያ የሆነው ሜቆሮት (Mekorot) መሥራች እና ዋና መሐንዲስ በመሆን አገልግሏል።
ከዓመታት በኋላም በ1950ዎቹ በአንድ ዕለት ኢንጂነር ሲምቻ ምርምር በሚያካሄድባቸው በረሃማ የእርሻ ቦታዎች መካከል ተገኝቶ የተክሎቹን ሁኔታ በመቃኘት ላይ እያለ በመድረቅ ላይ ከነበሩት ተክሎች መሐል የለመለመ እና በጥሩ ሁኔታ ያደገ አንድ ተክል ትኩረቱን ሳበው።
ኢንጂነር ሲምቻ በዙሪያው ካሉ ተክሎች ተለይቶ የለመለመውን ተክል ተጠግቶ መመልከት ጀመረ። በዚያ የእርሻ ስፍራ በተመሳሳይ ወቅት የተተከሉ ዛፎች ቢኖሩም በብልሽት ምክንያት የሚንጠባጠብ የቧንቧ መስመር አጠገብ ያለው ይህ ዛፍ ግን በተለየ መልኩ ጤናማ እና አረንጓዴ መሆኑን አስተዋለ።
ይህ ያልታሰበ ክስተት ውኃን በብዛት ከመጠቀም ይልቅ በትንሽ መጠን እና በቋሚነት በቀጥታ ወደ ተክሎች ሥር ማድረስ እጅግ ውጤታማ ዘዴ እንደሆነ የተገነዘበበት አጋጣሚ ፈጠረለት።

ሲምቻ ብላስ ከዚህ በመቀጠልም ይህንን በአጋጣሚ የተገነዘበውን የጠብታ መስኖ ወደታላቅ የፈጠራ ውጤት ለመቀየር ከልጁ ከየሻያሁ ብላስ ጋር በመሆን ምርምር ሲያካሄድ ቆየ።
ከዚያም የውኃ ግፊትን እኩል የሚያደርግ ማንጠባጠቢያ (Emitter) በመፈልሰፍ በ1965 ዓ.ም ‘ኔታፊም’ የተሰኘውን ኩባንያ አቋቁሞ የዓለምን ዘመናዊ ግብርና መለወጥ የቻለውን የጠብታ መስኖ ዘዴ በመላው አስራኤል ማስፋፋት ጀመረ።
ከዓመታት በኋላም ይህ የሲምቻ ብላስ ግኝት ውጤት የሆነ ዘዴ በተለይ የውኃ እጥረት ባለባቸው ሀገራት በአጭር ጊዜያት ተቀባይነት ማግኘት ቻለ።
የጠብታ መስኖ ዘዴ ካስገኛቸው ጥቅሞች መካከል ከሌሎች የመስኖ ዓይነቶች በተለየ ከ30% እስከ 70% የሚደርስ ውኃ መቆጠቡ ነው። ዘዴው በትነት የሚባክን ውኃ እንዳይኖር ያደርጋል።
በተጨማሪም አንድ ተክል ዘወትር የሚፈልገውን የውኃ መጠን ብቻ እንዲያገኝ ማስቻሉ ውኃ እና ማዳበሪያ በቀጥታ ወደ ተክሉ ሥር ስለሚደርስ የምርት መጠኑ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያድግ አስችሏል።
ባልታሰበ አጋጣሚ የተገኘው እና በዚህ መልኩ በአጋጣሚ በተገኘ የተበላሸ የቧንቧ ጠብታ መነሻነት የተፈጠረው የጠብታ መስኖ ዘዴ ዛሬ ላይ በእስያ፣ በላቲን አሜሪካ እና በተለይም በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ ትልቅ ጥቅም መስጠት የቻለ ታላቅ ግኝት መሆን ችሏል።
በዋሲሁን ተስፋዬ
#EBC #ebcdotstream #agriculture #DripIrrigation